ለቡና ጥራትም ሆነ በቡና ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል – የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር

ሀዋሳ፡ መስከረም 09/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የ2016 ዓ.ም የቡና ግብይት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 ዓ.ም ዕቅድ ማስፈጸሚያ የቀበሌ ግብረ ሃይል እና የላኪ አርሶ አደሮች የውይይት መድረክ በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር ተካሂዷል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ሚጁ ፤ ቡና ለጌዴኦ ማህበረሰብ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መሰረት ከመሆኑም ባሻገር ለሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ መሆኑን ተናግረዋል።

አስተዳዳሪው አክለውም የይርጋጨፌ ወረዳ  ማህበረሰብ የቡና አምራች እና አቅራቢ እንደመሆኑ ለቡና ጥራትም ሆነ በቡና ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ወረዳው 20ሺህ 980 ሄክታር በቡና የተሸፈነ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ምርት የሚሰጥ ቡና 17ሺህ 162 ሄክታር  መሆኑን  የተናገሩት የወረዳው ቡና እና ቅመማ ቅመም ልማት እና ግብይት ጽ/ቤት ኃላፊ  አቶ   አበራ አሰፋ፤ በወረዳው በሚገኙ 26ቱም ቀበሌዎች 33ሺህ 469 አርሶ አደሮች ቡና በማልማት ኑሯቸውን እየመሩ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።

የቡና ግዢ ከገበያ ማዕከል ውጪ መከናወን፣ ህግ ወጥ የቡና ዝውውር፣ የቡና ጥራት ቁጥጥር መላላት፣ በቂ የገንዘብ ብድር ያለማግኘት፣ በቴክኒክ ያልተፈቀደ ህገ-ወጥ ማሽን መበራከት እና ሌሎችም ችግሮች በ2016 ምርት ዘመን እንደነበሩ በውይይት መድረኩ በቀረበው ሰነድ ተመላክቷል።

በተጠቀሱ እና ሌሎች ችግሮች ዙሪያ በስፋት ውይይት ተካሂዶ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ በማስቀመጥ መድረኩ ተጠናቋል።

የቡና ጥራት ግብይት ዙሪያ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን በመለየት ችግሩን ለመፍታት በቀጣይ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ በውይይት መድረክ ከተገኙ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ሽፈራው ቃንቄ፣ አቶ ተፈራ ጅግሶ እና ሌሎችም ተናግረዋል።

ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን