የደቡብ ኢትዮጵያ… ከነሐሴ እስከ ነሐሴ !

ክፍል-ሁለት በዘላለም ተስፋዬ

ኢኮኖሚያዊና ምጣኔ-ሃብታዊ እምርታ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከምስረታው ጀምሮ በነበረው አንድ አመት ውስጥ ያሳካቸውን የሰላምና ጸጥታ፣ የልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የህግና የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት የክልሉን ተቋማት ለማጽናት የሄደበትን ርቀት ተመልክተናል፡፡ በዛሬው እትማችን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በሌሎች ዘርፎች የነበሩ ስኬታማ ተግባራትንና የገጠሙ ፈተናዎችን እንመለከታለን፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አጠቃላይ የመዋቅር ማሻሻያ በማድረግ ካስመዘገባቸው ስኬቶች መካከል የኢኮኖሚው ዘርፍ ነው፡፡ በተለይ ለቀጣዮቹ 7 ዓመታት ድርሻ ያለው የክልሉን የ“ብልጽግና ፍኖተ ካርታ” በማዘጋጀት አጸድቆ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ የ7ቱ ዓመት የብልጽግና ፍኖተ ካርታ ሲዘጋጅ፥ በእያንዳንዱ አከባቢ የሚገኘውን ጸጋ አሟጦ ማወቅ፣ ለመደገፍና ለመከታተል የሚያስችል በመሆኑ፤ የምሑራን አደረጃጀቶችን ከፌደራል፣ ከክልልና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የክልሉ ተወላጅ ምሑራን በጥናትና ምርምር ክልሉን አግዘው ፍኖተ ብልጽግናን እውን ማድረግ አስችሏል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች፣ ኮሌጆች፣ ተቋማትና የምርምርና ስርጸት ማዕከላት የክልሉን መንግስት የሚያግዙበትና የሚደግፉበት የአሰራር ስርዓት መዘርጋት፥ የተበተነ አቅም እንዳይኖር ለማድረግ የተወሰደው መፍትሔ ለክልሉ አንዱ የስኬት መገለጫ ነው፡፡

በግብርናው ዘርፍ የታየው ሁሉ አቀፍ እድገትና ልማት ለሌሎች የኢኮኖሚ አውታሮች ተደማሪ አቅም የፈጠረና አንቀሳቃሽ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በተለይም እንደ ሀገር የተጀመሩ የአረንጓዴ አሻራ ኢንሼቲቭ፣ የሌማት ትሩፋትና የበጋ መስኖ ስንዴ በአብነት ይጠቀሳል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ እንደ ክልል በአንድ ጀምበር 55 ሚሊዮን የተተከለበትና በሀገር ደረጃ 600 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀምበር በማሳካት የዓለም ሪከርድ ሆኖ ሲመዘገብ ክልሉም የራሱን ድርሻ አበርክቷል፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአንድ አመት ውስጥ በበልግና በመኸር 395 ሚሊዮን ችግኝ የተከለ ቢሆንም፥ ነገር ግን የክልሉን ቁልፍ ችግሮች በተለይም ናዳ፣ የመሬት መንሸራተት፣ ጎርፍና የአፈር ለምነት መፍታት የሚቻለው የክልሉን አከባቢዎች በአረጓዴ መሸፈን ሲቻል በመሆኑ፤ ይህን ግብ ለማሳካት በጋራ ስምምነት እየተሰራ ነው፡፡

በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናን ስፔሻላይዝድ አድርጎ ለማውጣት ያረጁ ቡናዎችን መጎንደል፣ አዳዲስ ቡናዎችን መትከል የተሻለ ውጤት ለማምጣት እያገዘ ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ እንሰት ለክልሉ ህዝብ የምግብ ዋስትና መሰረት በመሆኑ ከስራስር ሰብሎች አኳያ የእንሰት ልማቱን በማስፋፋት ለውጥ ለማምጣት ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡

በአርብቶ አደሩ አከባቢ የእንስሳት ሀብት ልማትን ማዕከል ያደረገ፥ የመኖና ጤና ምርታማነትን የሚያበለጽጉ ተግባራትን በመምራት ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በአንደኛ አመት የምስረታ በዓል ላይ አመላክተዋል፡፡

በዚህ 1 አመት ውስጥ ተራራን የማልማት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ የተወሰደበት ከመሆኑም በላይ፥ የተራሮች አናት በመራቆቱ አዳዲስ መንገዶች ከጥቅም ውጭ እየሆኑ፣ ለም የእርሻ መሬቶች ድጋይና አሸዋ እየለበሱ ነው፡፡ በጎርፍ እያታጠበ በመሆኑ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ምንም እንኳ የክልሉ የደን ሽፋን 23 በመቶ ቢሆንም አብዛኛው ተራሮች ገላጣና ስራ የሚፈልግ ለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡

የግብርና ኢኒሸቲቮች ከክልሉ ጸጋ አኳያ ውጤታማ ነበሩ ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ሌሎችም ከልማት ስራዎች አንጻር በተለያዩ ሴክተሮች የነበረው የአንድ አመቱ ጉዞ ውጤት የታየበት ሲሆን፥ በማዕከላት ስምምነት(በዲላ፣ ጂንካ፣ ኮንሶ፣ ሳውላ፣ ወላይታና አርባምንጭ ዲክላሬሽን) የተጣሉ ቁልፍና አበይት ግቦች ተቋማት እንዲያሳኩ የታቀዱ ተግባራት ውጤት አምጥተዋል፡፡

የክልሉን ጸጋዎች በዘርፍ በመለየት መንግስት፣ የግሉ አልሚ ባለሀብቶችና ኢንቨስተሮች ትኩረት እንዲያደርጉ በተለይም በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በ IT እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን ጸጋ ለይቶ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የክልሉን ህዝብ በማስተባብር አመቱን ሙሉ ጾሙን የማያድር መሬት እንዳይኖር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፥ የኑሮ ውድነት፣ የስራ እድል ፈጠራ ላይ የተሻለ እድል እንዲመጣ፤ ያለውን መሬት፣ ውሃ፣ ጉልበት አቀናጅቶ በመምራት ውጤት ማምጣት ተችሏል፡፡

ክልሉ ከቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ቢሆንም እነዚህ መዳረሻዎችን ማልማትና የቱሪስት መስህብነታቸውን ማሳዳግ ይገባል፡፡ መስህብ ስፍራዎችን ማልማትና መጠበቅ እንደዚሁ ከግሉ አልሚ ባለሀብት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ለማድረግ የተመራበት አግባብ በአንድ አመት ውስጥ ስኬታማ ነበር፡፡

በግብርና ምርት ተጨማሪ የግሉ ባለሀብት ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን በመፍታት፥ በማኑፋክቸሪንግ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ነባሩን ችግር በመፍታት፤ አዳዲስ ባለሀብቶች እንዲገቡ ለማድረግ የተሰራው ስራ ውጤት አምጥቷል፡፡ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ስራ በማስገባት የሚገጥማቸውን ቢሮክራሲና ማነቆ በመፍታት በግሉ ዘርፍ ያለውንም ችግር በመገምገም የተመራበት አግባብ በዘርፉ ለመጣው ውጤት ማሳያ ነው፡፡

ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠርና የልማት ፍላጎታቸውን ማሳካት የመንግስታት ተልዕኮ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፥ በከተማና በገጠር የስራ ዕድል የመፍጠር ትልምና የኑሮ ውድነት ማረጋጊያ ውጥን ስኬታማ የነበረ ቢሆንም ውስንነቶች ግን አልታጡበትም፡፡ ትልቁ የስራ እድል መፍጠሪያ አቅም ግብርና ቢሆንም በከተማና በገጠር ያለውን የኑሮ ውድነት የሚያረጋጋ ስራ እንዴት እንፍጠር የሚለው ጥያቄ አሁንም ዘላቂ ስራ የሚፈልግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ; ክህሎት መር ስራ እድል ፈጠራ ብቃት ባለው አግባብ እንዲመራ የተደረገበት ሂደት ከዘንድሮ እቅድ አኳያ ከሞላ ጎደል ስኬታማ ነበረ ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

የማህበራዊ ልማት ስኬታማነት

በማህበራዊ ልማት ዘርፍ በተለይ ባለፈው አንድ አመት ከትምህርት አኳያ የሚታየውን የውጤታማነት ችግር መቅርፍ የክልሉ መንግስት ቁልፍ አጀንዳ ነበር፡፡ የመጪውን ዘመን ሀገር ተረካቢ ዜጎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው የሚታየው የምዘና ስርዓትና የውጤት ስብራት ለመቅረፍ፥ ትምህርትን በህዝብ ተሳትፎና በዜግነት አገልግሎት ህዝቡን ቀጥተኛ ባለድርሻ በማድረግ መፍትሔ ለማምጣት ተሞክሯል፡፡

በትምህርት ስራ ላይ የህዝብ ተሳትፎ በመፍጠር የመማሪያ ክፍሎች መታደስ፣ በአንድ አመት ውስጥ በርካታ ትምህርት ቤቶች መገንባት፣ የትምህርት ግብዓት መሟላት፣ ወንበር ጠረጴዛ፣ ከምንም በላይ የመጽሐፍ አቅርቦት 1 መጽሐፍ ለ1 ተማሪ በሚል ኢኒሼቲቭ ለ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች መጽሐፍ ተደራሽ ማድረግ መቻሉ ትልቅ ስኬት ነው፡፡

የትምህርት ጥራት ባለቤት ዋናው መምህሩ በመሆኑ፥ ለመምህራን የአቅም ግንባታ ድጋፍ ማድረግና ያለባቸውን መሠረታዊ ችግር መፍታት ጤናማ ግንኙነት የፈጠረ ሲሆን፥ ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት፣ ትብብርና ስምምነት በማድረግ የተመራበት አግባብ ከሞላ ጎደል ውጤት አምጥቷል፡፡

የክልሉን ህዝብ ጤና ከተላላፊና ሌሎች በሽታዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተለይም ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲፈጠር ለማድረግ በተሰራው ስራ ውጤታማ አመት ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ አንዳንድ ከጤና ተቋማት አኳያ በፍጥነትና ጥራት ተደራሽ የመሆን ችግር ቢያጋጥምም፥ ነገር ግን ችግሮቹን ለይቶ ለመፍታት የተሄደበት ርቀት በበጎ የሚታይ ነው፡፡ መድሐኒት ቤቶች፣ የጤና መድህን፣ የጤና አገልግሎት ጥራት ያለው እንዲሆን ለማድረግ ከባለሙያዎች ጋር የጋራ መግባባት ላይ መድረስ መቻሉ የስኬት መገለጫ ነው፡፡

ያጋጠሙ ፈተናዎች

በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በመልካም አስተዳደር የታዩ ስኬቶች እንዲሁ አልጋ በአልጋ የተገኙ ባይሆኑም፥ ፈታኝ የሚባሉ ጉዳዮች ክልሉን ገጥመውታል፡፡ የተመዘገቡ ስኬቶች እንደ ስኬት ከተወሰደ የነበሩ ፈተናዎችና ውስንነቶች ትምህርት ሊወሰድባቸው የሚገባ ነው፡፡

ከዚህ አንጻር የመጀመሪያውና ትልቁ ውጤታማ የአመራር አንድነት ያለመኖር ችግር ፈታኝ የክልሉ መንግስት ተግዳሮት ነበር፡፡ ክልሉን ለመምራት ቃለ-መሐላ ፈጽሞ ኃላፊነት የወሰደ ኃይል ማንንም ሳይጠብቅ የራሱን ስራ ጉድለት እየሞላ ውጤታማ በሆነ መንገድ መምራት ሲገባ፥ የውስጥ አንድነት መላላት፣ ለጥርጣሬ በር መክፈትና ለውዥንብር ወሬዎች ሁኔታዎችን ማመቻቸት ክልሉ በሚፈለገው ልክ እንዳይጓዝ እንቅፋት የሆነ የአመራር ስርዓት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የዚህን ህዝብ ጥያቄ ተቀብሎ ምላሽ ለመስጠት ኃላፊነት የተጣለበት የዚህ ክልል አመራር፥ ምንም እንኳ በዚህ ውስጥ የተገኙ ጥቂት ቢሆኑም ተጽዕኖ መፍጠራቸው የማይቀር በመሆኑ ችግር ፈጣሪ የአመራር ስርዓት መፈጠሩ ጉልበትና አቅምን የጎተተ በመሆኑ ትምህርት ሊወሰድበት የሚገባ ነው፡፡

ሌላኛው ፈታኝ ችግር የነበረው የወጪ ፍላጎትና የክልሉ ገቢ ሚዛን መጣጣም ያለመቻል ፈታና ብዙ ነበር፡፡ በኢኮኖሚ ትልቁ ስኬት የውስጥ ገቢን ከፍ አድርጎ የወጪ ፍላጎትን ከ75 በመቶ በክልሉ ገቢ መሸፈን ቢሆንም፥ ገቢን ግን አሟጦ ያለመሰብሰብ ችግር በግልጽ ፈተና ሆኖ መጥቷል፡፡ ከዚህ አኳያ ያለው ተግዳሮት የወጪ ፍላጎትና የክልሉ የገቢ ሚዛን አለመጣጣም በአንዳንድ አካባቢዎች የግዴታ ወጪን (ደሞዝ) ጭምር መሸፈን ያልተቻለበት ሁኔታ አስከትሏል፡፡

ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ለመንግስት ገቢ ሊሆን የሚገባ ፍትሃዊ ገቢ፥ ግን ደግሞ የተሰወረ፣ የተደበቀ ገቢ አለ፡፡ በዛው ልክ አላስፈላጊ ወጪ በእጥፍ የናረበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ መዋቅሮች በእጅጉ ከመወጠራቸው ባለፈ የአንድ ወረዳ ወይም ዞን አመራርና ባለሙያ ቁጥር ከመጠን በላይ ተለጥጧል፡፡ ስራው ከሚፈልገው በላይ የተከማቸ ግን ደግሞ የወጪ ምንጭ እንጂ ገቢ የጠፋበት ሁኔታ በማስከተሉ ለክልሉ መንግስት ከፍተኛ ፈተና የደቀነበት አመት ሆኖ አልፏል፡፡