በ2016 ዓ.ም ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ስፖርት በርካታ ሁነቶችን ያካሄደችበት ዓመት ነው

በዓመቱ በእግር ኳስ ስፖርት የተከናወኑ አበይት የሆኑ ክንውኖችን መለስ ብለን ልናወሳችሁ ወደናል።

ኢትዮጵያን ወክሎ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የተሳተፈው ባህርዳር ከተማ በመጀመሪያው ዙር ቅድመ ማጣሪያ የታንዛኒያውን አዛም ክለብ በደርሶ መልስ አሸንፎ ከተመለሰ በኋላ በሁለተኛው ዙር ቅድመ ማጣሪያ የቱኒዚያውን ክለብ አፍሪካ በሜዳው አስተናግዶ 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ቢችልም ቱኒዚያ ላይ በተደረገው የመልስ ጨዋታ 3-0 በመረታቱ በድምር ውጤት 3-2 ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ የሆነበት ዓመት ነው የ2016 ዓ.ም።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ተብሎ ይጠራ የነበረው ውድድር ከአራት ዓመታት በኋላ ዘንድሮ የኢትዮጵያ ዋንጫ በሚል ስያሜ መመለስ የቻለው በዚሁ ዓመት ነበር።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ኢሳያስ ጅራ የካፍ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነው የተሾሙበት ዓመት ነበር 2016 ዓ.ም።

በዓመቱ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከተሰየሙት ሌሎች የሹመት ዜናዎች መካከል አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ ለአንድ ዓመት በሚቆይ ኮንትራት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙትም በዚሁ ዓመት መሆኑ አይዘነጋም።

በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት በተካሄደው የ2024ቱ የአፍሪካ ዋንጫ፥ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ፣ የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር እና የፊፋ ቴክኒካል ኤክስፐርት አብርሃም መብራቱ የአፍሪካ ዋንጫው የቴክኒካል ቡድን አባል በመሆን እንዲሁም ኮሚሽነር ተስፋነሽ ወረታ በካፍ የዳኞች ኮሚቴ አባል በመሆን ከኢትዮጵያ የተወከሉበት ዓመት ነበር።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ እና የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት ከመምራቱ በተጨማሪ በደቡብ አፍሪካ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መካከል ለደረጃ የተካሄደውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት መምራታቸው ይታወሳል።

አድዋን ለብዙሃን ለማስተዋወቅ ያለመ የእግር ኳስ ውድድር ፌስቲቫል በአሜሪካ አትላንታ “አድዋን ለኢትዮጵያ፣ ለትውልድ እንዲሁም ለመላው ዓለም በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደበት ዓመት ነበር የ2016 ዓ.ም።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የአሜሪካው ሜጀር ሊግ ተሳታፊው ዲሲ ዩናይትድ የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙበት ዓመትም ነበር።

ዲሲ ዩናይትድ ከፌዴሬሽኑ ጋር ከፈፀመው የመግባቢያ ስምምነት በተጨማሪ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብና ከኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ጋር ባደረጉት ስምምነት መሰረት የሸገር ደርቢ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካ ምድር የተካሄደው በዚሁ ዓመት መጨረሻ ሰሞን ነበር።

አንጋፋው የድሬዳዋ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳው፥ የሰው ሰራሽ ሳር ንጣፍ የተደረገለትም ዘመን ነው የዘንድሮው ዓመት።

ሽመልስ በቀለ ከ15 ዓመታት በላይ ካገለገለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ራሱን ያገለለበት ዓመት ነው አሮጌው ዓመት።

በዓመቱ በእግር ኳሱ ከተሰሙ አሳዛኝ ዜናዎች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በህትመትና በኤሌክትሮኒክስ (ሬዲዮ እና ቴለቪዥን) ብዙሃን መገናኛ ዘርፍ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን በመስራት ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ከዚህ ዓለም በሞት የተለየበት ዓመት ነው 2016።

በእግርኳሱ ሌላኛው አሳዛኙ ክስተት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የባህርዳር ከተማው የመሃል ሜዳ ስፍራ ተጫዋች የነበረው አለልኝ አዘነ በድንገት ሕይወቱ ያለፈበት ዓመትም ነበር።

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አስተናጋጅ በሆነችበት የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የኢትዮጵያው ተወካይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ የመጀመሪያውን ዋንጫ በማንሳት የሴካፋ ዞንን ወክሎ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስሊግ እንደሚሳተፍ ያረጋገጠው በዘንድሮው ዓመት መሆኑ አይዘነጋም።

በዓመቱ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከተከሰቱ አስገራሚ አጋጣሚዎች መካከል በሃገሪቱ እግር ኳስ የዳኝነት ታሪክ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ሁለት ጥንዶች ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ወጋየሁ ዘውዱ በውድድር ዓመቱ 12ኛ ሳምንት አዳማ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ያከናወኑትን የጨዋታ ግጥሚያ በጋራ የዳኙት በዚሁ የ2016 ዓ.ም ነው።

አዘጋጅ፡ ሙሉቀን ባሳ