ታላቁ ዲፕሎማሲያዊ ስኬትና ታላቁ ግድብ

በማሬ ቃጦ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተፈጥሮ ፀጋን በራስ አቅም የማልማት ተምሣሌት ነው፡፡ ይህ ለአለም የሚበቃ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ኖሯቸው ማልማት እና ዜጎቻቸውን ከድህነት ማውጣት ለተሳናቸው የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ አብነት መሆኑ እሙን ነው፡፡

እንደ ግብጽ ባረጀ ዘመን እሳቤ መቸንከር ባለንበት ዘመናዊው ዘመን የትም እንደማያደርስ ትልቅ መልዕክት ያዘለ ነው – የህዳሴ ግድባችን፡፡  ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ የታደለችውን የአባይን ውሃ ለብቻዬ ልጠቀም የሚለው ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ይመነጫል፡፡ ቅኝ ግዛት ዓላማው የሌላውን ሀብት መቀራመት፣ የሀብቱን ባለቤት ደግሞ በድህነት ማቆየት፣ አቅመ ቢስና ባሪያ ማድረግ ነው፡፡

ኢትዮጵያንና ሌሎች የተፋሰሱን ሀገራት ያገለለው እና ግብጽና ሱዳንን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ውል በፈንጆቹ 1929 እና 1959 ላይ መፈረሙ ይታወቃል፡፡ የዚህ አይነቱ አግላይ እና የቅኝ ግዛት ዘመን ውል ሊፈታ የሚችለው በምዕራባዊ እሳቤ ሳይሆን በአፍሪካ ነው፡፡ ከህዳሴው ግድብ ዲፕሎማሲና ድርድር ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ የጸና አቋምም ይኸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ  እምነት ግድቡ የአንድነትና የትብብር ምንጭ ይሆናል የሚል ሆኖ ቆይቷል፡፡

ድፍን 13 አመታት ተቆጠሩ፤ ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ግንባታ ሥራ ከተጀመረ፡፡ እዚህ ጋር ከጠንካራው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ጋር የተዳመረው የማድረግ አቅም የግብፅን ትርክት ተገዳድሮታል፡፡ አባይ የግብጽ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያና የሌሎችም ጭምር ነው የሚል ተግባራዊ እና ትርክት ቀያሪ ታሪክ በመላ ኢትዮጵያዊያን ተሠርቷል፡፡

የኢትዮጵያውያን ብርቱ የትብብር ክንድም ለዲፕሎማሲው ስኬት አይነተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ለ13 ዓመታት የዘለቀውን ዲፕሎማሲያዊ ጫናን የተቋቋመችውም በህዝቦቿ አንድነትና፣ በቁርጥ ቀን መሪዎቿ ብልሀት እንዲሁም በሀገር ወዳድ የዘርፉ ሊህቃንም ጭምር ነው፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ግብጽ የስም ማጥፋት እና የሀሰት ውንጀላዎች በኢትዮጵያ ላይ በከፈትችባቸው ወቅቶች የተካሄዱ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ድሎችን ማየት በቂ ነው፡፡

ግብፅ ገና ከጅምሩ ስለግድቡ መረጃ ይሰጠኝ፣ በገለልተኛ ቡድን ይጠና፣ በሶስተኛ ወገን ድርድር ይካሄድ  በሚል በተለያዩ ጊዜያት ራስ ወዳድ አቋም ስታንፀባርቅ ቆይታለች፡፡ ይህን ተከትሎ አለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድንና የሶስቱ ሀገራት የቴክኒክ ቡድን ጥናት አቅርቧል፡፡ ይሁንና ቡድኑ ያቀረበውን ሪፖርት ልትቀበለው አልወደደችም፡፡

አባይ የኔ ብቻ ነው የሚል ከእውነት የራቀ እምነት በመያዟ ምንም አይነት አሳማኝ ሳይንሳዊ አካሄዶች የማይዋጥላት ግብጽ ሌላ ሀሳብ አመጣች፡፡ ድርድሩ የጥቅም አጋሮቿ በሆኑት በአሜሪካና በአለም ባንክ በኩል ይሁንልኝ አለች፡፡

የአባይ ወንዝ ያለው በአፍሪካ ምድር ነው፡፡ ምንጩም ሆነ ግድቡ የሚገኙት ደግሞ በአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል በሆነችው በኢትዮጵያ ነው፡፡ ታዲያ በየትኛው መዘዘኛ ድርድሩ ከአፍሪካ ውጭ ሊሆን ይችላል!? መጥፎ የቅኝ ግዛት ልክፍት ካልሆነ በስተቀር፡፡

በመሆኑም አሜሪካም ሆነች የአለም ባንክ ሁለቱ ከታዛቢነት ያለፈ ሚና ሊኖራቸው አይገባም የሚል ፅኑ አቋም የያዘችው ኢትዮጵያ በቀረበው ሰነድ ላይ ፊርማዋን ሳታኖር ቀረች፡፡ይህን ተከትሎም የአሜሪካ  ፕሬዚዳንት  የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ግብፅ ግድቡን ታፈነዳዋለች ሲሉ ተደመጡ፡፡

ከዚህ በኋላ ግብጽ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ተደርጎ ማይታወቅ ሌላ ጉዳይ ይዛ ብቅ አለች፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት የግድቡን  ጉዳዩን ልያየው ይገባል የሚል ሀሳብ አቀረበች፡፡

በዚህም ቢሆን እውነትን የያዘችው ኢትዮጵያ ሁሉንም እንዳመጣጡ እየረታች ዲፕሎማሲያዊ ድሏን አጣጥማለች፡፡ ግብጽ ሆዬ አሁንም አልተሳካላትም፡፡

ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ባደረገቻቸው የሶስትዮሽ ድርድሮች እሰከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ ከሱዳን በኩል ይህ ነው የሚባል የከረረ ተቃውሞ ቀርቦባት አያውቅም። ይልቁን የኢትዮጵያን አቋም በተለያየ ግዜ ደግፋለች፡፡ በዚህ ምክንያት ግብጽ ሱዳን ስትተች ተስተውሏል፡፡

ግብፅ ከአረብ ሊግ እስከ አውሮፓ ህብረት፣ ከአሜሪካ እስከ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድረስ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲስተጓጎል ለማድረግ ደጅ ስትጠና ሰንብታለች፡፡ በቅርቡም ኢትዮጵያ ያለ እኔ በጎ ፈቃድ 5ኛ ዙር የውሃ ሙሌት እያከናወነች ነው ስትል ዳግም ጉዳዩ ለማይመለከተው የጸጥታው ምክር ቤት የተለመደውን ክሷን አቅርባለች፡፡

ኢትዮጵያ በጠንካራ መሪዎቿ ፊትአውራሪነትና በፍቀሯ በነደዱ ልጆቿ የተባበረ ክንድ የግድቡን ግንባታ በቀን ለ24 ሰዓታት በሳምንት ለሰባት ቀና ያለማቋረጥ ግንባታውን አቀላጥፈዋል፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁ የህዳሴ ግድብ የግንባታ ሥራ ከሞላ ጎደል መጠናቀቁን እና 3 ተርባይኖችም ኃይል ማመንጨት መጀመራቸውን ለኢትዮጵያዊያን አብስረዋል፡፡

ኢትዮጵያውን በአፍሪካ ታላቁን ግድብ ገንብተው ከጫፍ ደርሰዋል፡፡ ፍሬውን እያዩት ነው፡፡ ይህ ለሌላ ድል ያዘጋጃቸው እንደሆን እንጅ ረክተውም የሚቀመጡ አያደርጋቸውምና ታሪክ እየሠሩ ይቀጥላል፡፡