ሀዋሳ፡ ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዞኑ የታየውን አንፃራዊ ሠላም ወደ ዘላቂ ሠላም ለማሻገር የፖሊስ አመራሮችና አባላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጎፋ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ አስታወቀ፡፡
ፖሊስ ወንጀልን ከመከላከል ጎን ለጎን በልማት ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።
የጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኢንስፔክተር ታረቀኝ አጥናፉ የፖሊስ አመራርና አባላት ግምገማ ማጠቃለያ ላይ እንደተናገሩት በዞኑ በየደረጃው ባሉ የፖሊስ አመራርና አባላት ዘንድ የሚታዩ የአመለካከት፣ የተግባርና የስነ-ምግባር ችግሮችን በማረም ወቅቱን የሚመጥን አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ለመስጠት የፖሊስ አመራርና አባላትን በማብቃት ለተልዕኮ ዝግጁ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
በየደረጃው ባሉ የፖሊስ መዋቅሮች በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የታዩ ጉድለቶችን መለየታቸውን አንስተው፥ በተያዘው በጀት ዓመት ጉድለቶችን በማረም ጠንካራ ሥራዎችን በማስቀጠል ውጤታማ ተግባር ለማከናወን መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ፖሊስ ከወንጀልና ከቆሻሻ የፀዳ አካባቢ ለመፍጠር በልማት ሥራዎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ኢንስፔክተር ታረቀኝ ተናግረዋል።
የዞኑ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳግማዊ ዘሪሁን በበኩላቸው የፖሊስ አመራሮችና አባላትን ለቀጣይ ተልዕኮ የሚያዘጋጁ ተግባራት በትኩረት እየተሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ፖሊስ የማህበረሰቡ አካል እንደመሆኑ ወንጀል በመከላከል የሕዝቡ ደህንነት ከማስጠበቅ ባሻገር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
በዞኑ የታየውን አንፃራዊ ሠላም ወደ ዘላቂ ሠላም ለማሻገር የፖሊስ አመራሮችና አባላት ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ አንስተዋል።
የሣውላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ደሳለኝ ጩቱሎ በበኩላቸው የፖሊስ ዋናው ተግባር ወንጀልን በመከላከል የሕዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ መሆኑን ገልጸው፣ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥር አደጋ መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር ለማ ላቾሬ ፖሊስ ወንጀልን ከመከላከል ጎን ለጎን በልማት ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የጎፋ ዞን ፖሊስ አመራሮችና አባላት “በጀግንነት መጠበቅ፤ በሰብዓዊነት ማገልገል” በሚል መሪ ቃል በሣውላ አጠቃላይ ሆስፒታል የጽዳት ዘመቻም አካሂደዋል።
እንደሀገር ጽዱ አካባቢና ጽዱ ተቋም ለመገንባት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ተግባራዊ ለማድረግ የፖሊስ አመራሮችና አባላት የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆናቸው ተገልጿል።
ፖሊስ ሰላምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ከተማዋን ጽዱ፣ ውብና ማራኪ ለማድረግ ያለበትን ማህበራዊ ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
የሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ወንደሰን ካሳሁን የፖሊስ አመራርና አባላት ላደረጉት የጽዳት ዘመቻ ምስጋና አቅርበዋል።
ከጽዳት ዘመቻው ጎን ለጎን በሣውላ ፖሊስ ጣቢያ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ጉብኝት ተደርጓል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
አዲሱ ትውልድ ጀግኖች አባቶቻችን በክብር ያቆዩልንን ሀገር የመጠበቅ ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ መነቴ ሙንዲኖ ገለፁ
የፀጥታ አካላት በየዘመኑ የአገር ክብርና ሉአላዊነትን በማረጋገጥና መስዋዕትነት በመክፈል እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ ተናገሩ
ወባን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጸጋዬ ማሞ ተናገሩ