የጌዴኦ ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አሰጣጥና የካዳስተር ሥራ አፈፃፀም ዙሪያ ከዘርፉ ባለድርሻዎች ጋር የግምገማ መድረክ አካሂዷል፡፡
የዞኑ ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ረድኤት ክፍሌ በመድረኩ በዞን ደረጃ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም ከሚያመነጩ መዋቅሮች የዲላ ከተማ ቀዳሚ መሆኑን በመጥቀስ በከተማው የካዳስተር ምዝገባ ሥራ ከ2009 ዓመተ ምህረት ጀምሮ በትኩረት እየተከናወነ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ የማዘጋጃ ቤቱ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የካዳስተር ምዝግባ ሂደት፣ በምዝገባው ሥራ የተስተዋሉ ማነቆዎችን ግምገማ በማድረግ የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የተዘጋጀ መድረክ ነው ብለዋል፡፡
የካዳስተር ምዝገባ ከተማውን በመረጃና በእውቀት ለመምራት የሚያስችል መሆኑን የገለጹት አቶ ረድኤት ይህም በግብር አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ከማስቀረት አኳያ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ከከተማው መስፋፋት ጋር ተያይዞ በካዳስተር ያልተካተቱ ይዞታዎችን ለይተው በመመዝገብ ማደራጀት እንደሚያስፈልግ የገለጹት የመምሪያው ኃላፊ፤ የካዳስተር ምዝገባ ሥርዓትን በማዘመን ለተገልጋዮች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የመምሪያው ምክትልና የካዳስተር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወላሶ የካዳስተር ሥራ አፈፃፀምን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፤ ዘርፉ ከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዳለው በመግለጽ የመረጃ አያያዝን ከማዘመን እንዲሁም ምቹ የሥራ ቦታ ከመፍጠር ጀምሮ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ባለሙያዎች በበኩላቸው በተቀመጠው መመሪያ መሠራት ሥራቸውን እንዳያከናወኑ አስፈላጊው ግብዓት በተገቢው ሁኔታ አለመሟላቱን ጠቅሰው በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስቀረት የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በብዝሃነት ውስጥ የሚንፀባረቁ የመረዳዳትና የአብሮነት በጎ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና የየዞን ከፍተኛ አመራሮች በሣውላ ማረሚያ ተቋም አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና ልየታ ተካሄደ