ሀዋሳ፡ ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቅርቡ በሀገር ደረጃ የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ተከትሎ በተለያዩ ምርቶች ላይ የተስተዋለውን የዋጋ ጭማሪ ለመከላከል እየሠራሁ ነው ሲል የይርጋጨፈ ከተማ አስተዳደር የንግድ እና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ገልጿል።
በዚህም የተለያዩ ያለአግባብ ምርቶች ላይ ዋጋ በጨመሩ የጅምላ እና የችርቻሮ ሱቆች ላይ እርምጃ እስከ መውሰድ መደረሱን አመላክቷል።
የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ እና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን አሰፋ እንደገለፁት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ በተፈጠረው ከምንዛሪ ለውጥ ጋር አያይዞ የተወሰኑ የምግብ ነክ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መስተዋሉን ገልፀዋል።
በተለይ በምግብ ዘይት፣ በሩዝ እና በስኳር ምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ መስተዋሉን በመጥቀስ በዚህም ምርቶችን የመደበቅ እና የመሰወር ሥራ እየተስተዋለ እንደነበር በተደረገው የኢንስፔክሽን ክትትል እና በህዝብ ጥቆማ የተደረሰባቸው 10 የጅምላ እና ከ20 በላይ የችርቻሮ በአጠቃላይ ከ30 ሱቆች በላይ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል።
ለዚህም አስቀድሞ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ እና ምርት የመሸሸግ ሥራ እንዳይኖር ለማድረግ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይት በማድረግ ጤናማ የገበያ ሂደት እንዲፈጠር መግባባት ላይ ተደርሶ እየተሠራ ቢሆንም ያለአግባብ ጭማሪ እንዲኖር የሚሠሩትን ከማስጠንቀቅ አልፎ እርምጃ እስከመውሰድ መደረሱን ገልፀዋል።
በጽ/ቤቱ የኢንስፐክሽን እና ሬጉሌሽን ባለሙያ ወ/ሮ አስቴር ክፍሌ በበኩላቸው በየእለቱ የገበያ ክትትል እንደሚያደርጉ በመግለፅ አሁን ላይ በየሱቆቹ የእያንዳንዱ ምርት ዋጋ ውጪ እና ውስጥ እንዲለጠፍ በማድረግ የገበያ ግልፀኝነትን በመፍጠር ሥራ ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ካነጋገርናቸው የንግዱ ማህበረሰብ አባላት መካከል አቶ መሉቀን ወንደፍሬ እና አቶ ዘነበ ደማ የጅምላ ምርት አቅራቢዎች ሲሆኑ በተደረገዉ የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ በዘይት፣ ስኳር እና መሳሰሉት ምርቶችን ከሚያስመጡበት ቦታ ላይም ጭማሪ እንደነበር በመጥቀስ በከተማውም መሰል ችግሮች ተስተውለው እንደ ነበር ተናግረዋል።
ከንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ጋር በነበራቸው ውይይት መተማመን ላይ በመድረሳቸው በተጠቀሱ ሸቀጦች ላይ መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ መደረጉን በመግለፅ አሁን ላይ ለምርቶች ከሚመጣበት ዋጋ አንፃር የዋጋ ተመን አውጥቶ ለጽ/ቤቱ በማሳወቅ እንደሚለጥፉ ገልፀዋል።
ዘጋቢ: አብዶ አያላ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ