በአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ሰብሎች ልማት ከ41 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሠብሰብ መቻሉ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ሰብሎች ልማት በበጀት አመቱ ከ41 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሠብሰብ መቻሉን የጋሞ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

በበጀት አመቱ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡንና በቀጣይ የሚታዩ ውስንነቶችና ጉድለቶችን በማረም ረገድ ሊሰራ እንደሚገባ ተገልጿል።

የጋሞ ዞን ህዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር መርሐ ግብር 10ኛ አመት የስራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ጉበኤውን እያከናወነ ነው።

የጋሞ ዞን ም/ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ ለምክር ቤቱ አባላት የ2016 በጀት አመት አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፥ የሰብል ልማት ሽፋንና ምርታማነትን ለማሰደግ በርካታ ተግባራት መከናወኑን ጠቁመው፥ በበጀት አመቱ በአዝዕርትና በሆርቲካልቸር ሰብሎች 41 ሚሊዮን 173ሺ 131 ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ የአፈርን ለምነት ለመጠበቅ  እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ በደንና አከባቢ ጥበቃ ልማት ስራዎች ሀገር በቀል ችግኞች ላይ ትኩረት በመስጠት 38 ሚሊዮን 404 ሺ814 ችግኝ መተከሉን ተናግረዋል።

ህጋዊና ፍትሀዊ የንግድና ግብይት ስራዎችን በማጠናከር የኢንስፔክሽን ስራዎች መከናወናቸውንና የኤክስፖርት ምርት ግብይት 1ሺህ 241 ቶን ቦሎቄና 1ሺህ 209 ቶን የማሾ ምርት ለማእከላዊ ገበያ መቅረቡን ገልጸዋል።

የዞኑ የንጹህ መጠጥ ውሀ ሽፋንን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት ቢከናወንም የውሀ ሽፋኑ በገጠር 46 ነጥብ 5 ከመቶ በከተማ 56 ነጥብ 5 ከመቶ በከማካይ 48 ነጥብ 6 ከመቶ መሆኑን ጠቀሰው በቀጣይ ሽፋኑን ለማሳደግ ሰፊ ስራ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።

የዞኑ የገቢ አፈጻጸም በበጀት አመቱ ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤቶች 3 ቢሊዬን 265 ሚሊዬን 191 ሺህ 62 ብር ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን ከጤና ተቋማትና ከትምህርት ቤቶች 294 ሚሊዬን 063 ሺ 150 ብር ለመሠብሰብ መቻሉን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

በቀጣይ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠልና ሊሻሻሉ የሚገቡ ተግባራትን የእቅድ አካል በማድረግ መስራት እንደሚገባ ለም/ቤቱ አብራርተዋል ።

ዘጋቢ ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን