የዳውሮ ብሄረስብ ማንነት መገለጫ የሆነውን የዘመን መለወጫ “ቶኪ ቤኣ” በዓል የፊታችን ነሐሴ 29 አና 30/2016 ዓ.ም ለሁለት ተከታይ ቀናት ለማክበር ከሁለት ወር በፊት አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን የተናገሩት የዞኑ ባህል፣ በቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ደምሴ ናቸው።
እንደ ኃላፊው ገለፃ “ቶኪ ቤኣ” የጥጋብ፣ የአብሮነት ምልክት፣ የእርቅ፣ የሠላምና የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን ተናግረው፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ የሚገኙ የብሄረሰቡ ተወላጆች የሚሰባሰቡበት እንዲሁም የተጣሉት የሚታረቁበት በዓል መሆኑን አብራርተዋል።
“ቶኪ ቤኣ” ስናከብር የዳውሮ ወግ፣ ባህል እንዲሁም የተለያዩ ቅርሶችን ለዓለም የምናስተዋውቅበት መድርክ ጭምር መሆኑን አቶ ፍቃዱ አስረድተዋል።
በበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓት ላይ እንዲታደሙ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የዞኑ ተወላጆችን ጨምሮ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች በክልሉ የሚገኙ የዞን አስተዳዳሪዎች፣ ሚኒስቴሮች፣ የወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ካምባታና ከኦሮሚያ ክልል የጅማ ዞንና የደዶ ወረዳ አስተዳደር እና ሌሎችም በርካታ እንግዶች እንደሚገኙ ተገልጿል።
የዳውሮ ብሄረሰብ መገለጫ “ቶኪ ቤኣ” በዓልን አስመልክቶ በተለያዩ ምሁራን ጥናታዊ በጽሑፎች እንደሚቀርቡና አጠቃላይ ይዘቱን ለተቀረው ዓለም እንዲታውቅ በተለያዩ ሚዲያዎች በበዓሉ ተገኝተው እንዲዘግቡ ጥሪ መደረጉንም የመምሪያው ሃላፊ አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶች መልካም መስተንግዶ ተደርጎላቸው እንዲሁም ያለአንዳች ፀጥታ ችግር በሠላም ወደየአካባቢያቸው እንዲመለሱ የዞኑን ማዕከል ታርጫ ከተማን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች አስፈላጊ ዝግጅት መጠናቀቁን አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በቅንጅትና በጥምረት መስራት እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ
አካባቢን በመጠበቅና በማጽዳት ምቹና ጽዱ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሁሉም የድርሻውን ልወጣ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳሰቡ
ግለሰባዊ ነጠላ ትርክቶችን በጋራ በመታገል በመደመር እሳቤ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ