የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወኑ እንደሚገኙ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወኑ እንደሚገኙ የጋሞ ዞን ህዝብ ምክር ቤት ገለጸ፡፡

የጋሞ ዞን ህዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር መርሀ ግብር 10ኛ አመት የስራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ጉበኤ አርባምንጭ ከተማ እያከናወነ ይገኛል።

የጋሞ ዞን ህዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሪት አለሚቱ ዮሴፍ የዞኑን ምክር ቤት 4ኛ ዙር መርሀ ግብር 10ኛ ዓመት የስራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ጉባኤን በንግግር ሲከፍቱ እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት አመት የዞኑን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል።

በየተቋሙ የሚታዩ ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን በመታገል በዞኑ ዘላቂ ልማትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከእጅ መንሻ የጸዳ አገልግሎት በመስጠት ቀልጣፋና ውጤታማ ተቋም መፍጠር የሁሉም ሀላፊነት ሊሆን እንደሚገባም በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል።

የህዝብና የመንግስት ሀብት ለታለመለት አላማ እንዲውል በኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ ሀይል አበረታች ተግባራት ቢከናወኑም ሰፊ ቀሪ ስራ መኖሩንና ህግ አውጪው፣ አስፈጻሚውና ህግ ተርጓሚው የየራሱን ድርሻ በተገቢው መወጣት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል “አንድ መጽሀፍ ለአንድ ተማሪ” በሚል መሪ ቃል እየተከናወነ የሚገኘው ንቅናቄ እንደ ዞን የተሳካ መሆኑን የሚጠቅሱት ዋና አፈ ጉባኤዋ፤ የጤና መሰረተ ልማት በአግባቡ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን የክትትልና ቁጥጥር ስራውን ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።

የረዥም ጊዜ የዞኑ ህዝብ ጥያቄ የነበረው የጋሞ ቴሌቪዥን መደበኛ ስርጭት መጀመሩና የእግር ኳስ መፍለቅያ ለሆነው ዞን የሚመጥን ደረጃውን የጠበቀ ስታድየም ግንባታ የመሠረት ድንጋይ መቀመጡ የዛሬውን ምክር ቤት ጉባኤ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

በጉባኤው የዛሬ ውሎ የዞኑ አስተዳደር ም/ቤት የ2016 ማጠቃለያ ሪፖርትና የ 2017 ዕቅድ፤ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያለፈው በጀት አመት ሪፖርትና እቅድ ቀርቦ የሚጸድቅ ሲሆን የ2017 በጀት አመት ረቂቅ የበጀት አዋጅ ላይ ም/ቤቱ ተወያይቶ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን