የሰለጠነ የጤና ባለሙያ ለማፍራት በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ የሚዛን አማን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አስታወቀ

በኮሌጁ በንድፍና በተግባር የሚሰጠው ስልጠና ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል እንደሆነም ተማሪዎች ገልጸዋል።

የሚዛን አማን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብቸኛና የሰለጠነ የጤና ባለሙያን በማፍራት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ የሚገኝ ተቋም መሆኑን የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ፀጋዬ አትርሴ ተናግረዋል።

ኮሌጁ የአርብቶ አደር የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በማሰልጠን የመማር ማስተማር ሥራን የጀመረ ሲሆን ባለፉት 14 ዓመታት 9 ሺህ 86 የተለያዩ የጤና ባለሙያዎችን አስመረቆ ለህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት እንዲሰጡ ማደረጉንም ዲኑ ገልፀዋል።

በክልላችን መካከለኛ የጤና ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ የሚዛን አማን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ከመሆኑም በተጨማሪ የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ እንደሚገኝም አቶ ፀጋዬ ተናገረዋል።

የኮሌጁ ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን በተግባር ተደግፎ በመማር ውጤታማ እንዲሆኑ እየሰራ እንደሚገኝና የማህበረሰብ ፋርማሲን በመክፈት በህብረተሰቡ ላይ የሚታየውን የመድኃኒት ዋጋ መናር ጫናን ለመቀነሰ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል ዲኑ።

ተወዳደሪና ብቁ በዕውቀት የተገነቡ ተማሪዎችን በማፍራት ለማህበረሰቡ በቂ አገልግሎትን የሚሰጥ ባለሙያን ለማፍራት እየተሰራ እንደሚገኝ የአካዳሚ ጉዳዮች ዲን አቶ ሰብስቤ ኤሊያስ ገልፀው የአቅም ማነስ ላለባቸውም ልዩ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ወደ ኮሌጁ የሚመጡ ተማሪዎች በሙያቸው ውጤታማ እንዲሆኑ በጤና ጣቢያና በሆስፒታሎች የተግባር ትምህረት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን የድንገተኛ ህክምና ትምህርት ክፍል አስተባባሪ መምህር መላኩ ስንታየሁ ተናግረዋል።

ካነጋገርናቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ኤልዳና ወንዱ፣ መቅደስ አድጓቸውና ተማሪ ገረመው ማቴዎስ በሰጡት አስተያየት በኮሌጁ ከሚያገኙት ዕውቀት በተጨማሪ ወደማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ሙያዊ ስነ ምግባራቸውን ጠብቀው ማገልገል የሚያስችላቸውን ግንዛቤ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አብዳሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን