ሀዋሳ፡ ነሐሴ 22/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለ2016/17 መኸር ወቅት የእርሻ ስራቸው ማዳበርያ ባለመቅረቡ መቸገራቸውን የቡርጂ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡
የዞኑ ግብርና መምሪያ በበኩሉ አርሶአደሮች የሚያነሱት ቅሬታ ተገቢ መሆኑን በማመን ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
አርሶ አደር ጨሜ ጨቶ እና ሾጋ አኖ የሐርዎንጄና የሬለያ ጎቼ ኩሮ ቀበሌ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ለመኸር ወቅት የማሳ ዝግጅት አጠናቀው መዝራት እንዳይጀምሩ የማዳበሪያ አለመቅረብ የአዝመራ ወቅቱን እንዳይጠቀሙ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡
ማሳችን ማዳበሪያ የለመደ በመሆኑ ያለ እሱ ምርት አይታሰብም ያሉት አርሶ አደሮቹ መንግሥት የዘር ወቅት ሳያልፍ በአፋጣኝ እንዲያመጣላቸውም ጠይቀዋል፡፡
አቶ ህርቦ ቤጦ የቡርጂ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው ከግብአት አቅርቦት ጋር ተያይዞ አርሶ አደሮች የሚያነሷቸው ቅሬታዎች ትክክል መሆኑን አንስተዋል፡፡ 10 ሺህ 500 ኩንታል Npsb እና 5 ሺህ 500 ዩሪያ የታቀደ ቢሆንም እስካውን የደረሰው 4 ሺህ 32 ኩንታል ዳፕና 420 ኩንታል ዩሪያ ብቻ በመሆኑ ካለው ፍላጎት ጋር መጣጣም ባለመቻሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየተሠራ እንደሆነ ያነሱት ኃላፊው ክልሉ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ማዳበሪያ ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉና ለአርሶአደሮችም የዘር ወቅት በመሆኑ ያላቸውን አማራጮች ሁሉ እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥራ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ዮሴፍ ቶልኬ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በቅንጅትና በጥምረት መስራት እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ
አካባቢን በመጠበቅና በማጽዳት ምቹና ጽዱ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሁሉም የድርሻውን ልወጣ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳሰቡ
ግለሰባዊ ነጠላ ትርክቶችን በጋራ በመታገል በመደመር እሳቤ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ