ሀዋሳ፡ ነሐሴ 22/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የታክስ ህግ ተገዥነትን በማስፈንና የታክስ ስወራንና ማጭበርበርን በማስቀረት የገቢ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት ለደረጃ ”ሀ” እና ”ለ” ግብር ከፋዮች በታክስ ህግና ተገዥነት እንዲሁም በሂሳብ መዝገብ አቀራረብ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል።
በመድረኩ የተገኙት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ፀጋነሽ ዮሐንስ ግብር የዜጎችን የመልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ገልፀው ሆኖም በግብር አሰባሰብ ወቅት በታክስ ተገዥነትና በሂሳብ መዝገብ አቀራረብ ላይ ከፍተኛ ጉድለቶች እንደሚስተዋሉ ገልፀዋል።
በተለይም ለህግ ተገዥ ሆነው ግብራቸውን የሚከፍሉ ታማኝ ግብር ከፋዮች እንዳሉ ሁሉ ደረሰኝ የማይቆርጡ፣ ግብይት ያለ ደረሰኝ የሚከውኑ፣ አላግባብ ተመላሽ የሚጠይቁና፣ መክፈል ከሚገባቸው በታች ግብር የሚከፍሉ መኖራቸው በጥናት በመለየቱ ይህም በመንግስትና በህዝብ ላይ የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ ተከተል በበኩላቸው በግብር ዙሪያ የህብረተሰቡን ንቃት ማሳደግ ለነገ የማይተው ጉዳይ ነው ብለዋል።
የሀዲያ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ መሳይ ተስፋዬ ለግብር አሰባሰቡ ማነቆ የሚሆኑና ህግን በሚተላለፉ አካላት ላይ የሚውሰዱ ርምጃዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው ህብረተሰቡ ከባለድርሻ አካላት ጎን በመሆን ህገ-ወጦችን በማጋለጥና ጥቆማ በመስጠት የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በሰጡት አስተያየት ግብርና ታክስን መክፈል የሀገር ወዳድነት መለኪያ መሆኑን አንስተው በአሰባሰብ ውቅት የሚያጋጥሙ ችግሮች ዙሪያ ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባና ለታክስ ህግ ተገዥነት መስፈን ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የከተማው ገቢዎች ጽ/ቤት በተያዘው 2017 በጀት ዓመት ከ2 ቢሊዮን 550 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱም ተመላክቷል።
ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ