መልካም ሥነ ምግባር የተላበሰ፣ ርህሩህና ተንከባካቢ የጤና ባለሙያ በመፍጠር ለተገልጋዩ ህብረተሰብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰራ የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 21/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) መልካም ሥነ ምግባር የተላበሰ፣ ርህሩህና ተንከባካቢ የጤና ባለሙያ በመፍጠር ለተገልጋዩ ህብረተሰብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰራ የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ገልጿል፡፡

የመምሪያው የጤና ቡድን ከዲላ ዙሪያ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ጋር በመሆን በሚችሌ ኡዶ ጤና ጣቢያ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን የመስክ ጉብኝት አድርገዋል።

በመስክ ምልከታው ላይ ገለፃ ያደረጉት የጤና ጣቢያው ኃላፊ አቶ ምህረቱ ዳያሶ በጤና ጣቢያው ከመደበኛ ጤና አገልግሎት በተጨማሪ በወሊድ ምክንያት ወደ እናቶች ማቆያ ለሚገቡ ከምግብ ዝግጅት ያለፈ ያሉበት ስፍራ  የቤት ያህል እንዲሰማቸው በጤና ባለሙያዎች ትብብር የጓሮ አትክልት፣ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ቀይስርና ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን ከማልማትም ባለፈ የዶሮ እርባታ በጤና ጣቢያው ለዚሁ አላማ ተዘጋጅቶ ይገኛል።

 ለህብረተሰቡ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት፣ ጽዱ ቀበሌ ለመፍጠርና ህብረተሰቡ የማሕበረሰብ ጤና መድሕን ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተሰጠው ትምህርት ለውጥ መታየቱን አስረድተዋል።

ሀብታሙ አለማየሁ፣ ወሰን እንዳለማውና ሌሎችም  በጤና ጣቢያው ወደ ተቋሙ ለሚመጡ ተገልጋዮች የጤና አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የተለያዩ የጤና አጠባበቅ ትምህርት እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የወረዳው ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አበባየሁ ማርቆስ በእናቶች በወሊድ አገለግሎት የተሰሩ ሥራዎች፣ ወደ ማቆያ ለሚገቡ እናቶች ከጓሮ አትክልቶችን በመትከል ምግብ ከጓሮ እንዲጠቀሙ  የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው ከተለያዩ ጤና ጣቢያዎች የተወጣጡ በመስክ ምልከታ መሳተፋቸው ምርጥ ተሞክሮ እንዲሰንቁ በማሰብ ነው ብለዋል፡፡

በጉብኙቱ የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያን ወክለው የተገኙት  አቶ አዲሱ ኩኡ የሚችሌ ኡዶ ጤና ጣቢያ በወረዳው ካሉ ጤና ጣቢያዎች ግንባር ቀደም መሆኑን ጠቅሰው ይህን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ለማስፋት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ቀበሌውን  ከዓይነምድር የጸዳ ለማድረግ በተሰራው ስራ ሙሉ አከባቢውን ጽዱ ማድረግ መቻሉን ኃላፊው ጨምሮ አስረድተዋል፡፡

የጤና ጣቢያው ለአገልግሎት መጥተው አስተያየት የሰጡት ተገልጋዮችም በተቋሙ እየተሰጠው ባለው አገልግሎት ደስተኞች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን