ሀዋሳ፡ ነሐሴ 21/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክረምት የበጎ ፍቃድ አግልግሎት ድጋፍ በማግኘታቸው መደሰታቸውን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡
የልዩ ወረዳው ወጣቶች በፌዴሬሽን፣ በማህበርና በሊግ በመደራጀት በክረምት የበጎ ፍቃድ አግልግሎት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን ከመደገፍ በሻገር በአካባቢያዊና ሀገራዊ የልማትና ሰላም ጉዳዮች በንቃት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተጠቀሚ ከሆኑ የልዩ ወረዳው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ወ/ሮ መዲና መሀመድና ከዲጃ ከዲር ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩበት ቋሚ ስራ የሌላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመዳረጋቸው የአልባሳትና የመገልገያ ቁሳቁሶች ድጋፍ በበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች እንደተደረገላቸው ተናግረዋል፡፡
ሌላኛዋ ወ/ሮ ሉባባ ሸምሱ በልዩ ወረዳው የሌንጫ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የአእምሮ ታማሚ ልጃቸውን ጨምሮ 4 ልጆችን ያለአባት በማስተዳደር ላይ ከመሆናቸውም በተጨማሪ መኖሪያ ቤታቸው በማርጀቱ ለብርድና ለፀሀይ ተጋልጠው መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ በልዩ ወረዳው አስተዳደር፣ በአካባቢው ማህበረሰብና በበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ድጋፍ የአዲስ ቤት ግንባታ እየተከናወነላቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡
ለተደረገላቸው ድጋፍም አስተያየት ሰጪዎቹ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ፡፡
ወጣት ሰይድ አህመድ በልዩ ወረዳው የፈረጀቴ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን በክረምቱ ወራት በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች በንቃት በመሳተፍ ላይ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ይህም ጊዜውን በአግባቡ ማህበረሰቡን ሊጠቅሙ በሚችሉ ስራዎች በማሳለፍ ትልቅ የአእምሮ አርካታ እንደሰጠው አስረድቷል፡፡
ወጣት ረቢዕ ሚፍታ የቀቤና ልዩ ወረዳ ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ሲሆን ማህበሩ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም ከልዩ ወረዳው ሰራተኛና ማህበራዊ አገልግሎት፣ ወጣቶችና ስፖርት፣ ሴቶችና ህፃናት፣አስተዳደር ጽ/ቤቶች እንዲሁም ከሌሎችም ተቋማት ጋር በመቀናጀት በርካታ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ማከናወኑን ተናግሯል፡፡
ማህበሩ በተያዘው የክረምት ወራት ብቻ የ5 አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ ማከናወኑን የገለፀው ወጣት ረቢዕ በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 50 ሺህ ብር ከአባላቱና ከለጋሾች በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረጉንም ገልጿል፡፡
በችግኝ ተከላ፣ በመንገድ ደህንነት እንዲሁም በሌሎችም ሀገራዊና አካባቢያዊ የልማትና ሰላም ጉዳዮች በንቃት በመሳተፍ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆናቸውን ወጣት ረቢዕ ተናግሯል፡፡
የልዩ ወረዳው ወጣቶችን በማህበር፣ በፌዴሬሽንና በሊግ ማህበራት እንዲደራጁ በማድረግ በ14 ዘርፎች ልዩ ልዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የቀቤና ልዩ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጁሃር ጀማል ናቸው፡፡
በክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት፣ በችግኝ ተከላ፣ በፅዳትና ውበት፣ በመንገድ ደህንነትና በሌሎችም የበጎ ፈቃድ አገለግሎት ስራዎች ከ40 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ 62 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን፣ አጋዥ ድርጅቶችንና ተቋማትን በማስተባበር እየተሰራ ባለው በዚህ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገለግሎት ከመንግስት ይወጣ የነበረውን ከ22 ሚሊየን ብር በላይ ለማዳን እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ጁሃር ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ