በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች እየተከናወነ ያለው የክረምት በጎ ፈቃድ ዜጎችን በተጨባጭ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል  – ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 21/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሁሉም አከባቢዎች እየተከናወነ ያለው የክረምት በጎ ፈቃድ ዜጎችን በተጨባጭ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገልጹ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተደድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እና በኢፌዲሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የተመራው ልዑክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያዊ ህዝቦች ክልል በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ የአቅመ ደካሞችን የቤት ግንባታ አስጀምረዋል።

የኢፌዲሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ መንግስት አካታች ማህበራዊ ልማት ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ዘርፈ ብዙ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በሀገር ደረጃ በጣም ሰፋፊ የሆኑ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሆነ የገለፁ ሚኒስትሯ በመተባበርና በአንድነት የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ እንደሚቻልም አብራርተዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከGGGI ከተሰኘ አለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ለቤቶቹ ግንባታና ለቤት ቁሳቁስ ግዥ ከ12 ነጥብ 5 ሚልዮን ብር በላይ በጀት እንደተመደበም ሚኒስትሯ  ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለ150 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉም ተመላክቷል።

በክልሉ በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ ተግባር 540 ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች ሰርቶ ለማስረከብ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራ እንደሆነም ተጠቁሟል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው በዞኑ በለውጡ መንግስት መሪነት እየተከናወነ የሚገኝ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት የሚያሰመሰግን እንደሆነ ጠቁመዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የኢፌዲሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በክልሉ ስላደረገው የአቅመ ደካሞች ቤት መስሪያ እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በክልሉ ህዝብና መንግስት ስም አመሰግነዋል።

በመርሃግብሩ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና የታርጫ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና የከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ልዑኩ በወላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ ዳውሮ ታርጫ ካምፓስ የችግኝ ተከላ መርሃግብርም አካሂደዋል።

ዘጋቢ፡ እታገኝ ዘነበ – ከዋካ ጣቢያችን