ጥራቱን የጠበቀ ማር ለወጪ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 21/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ጥራቱን የጠበቀ ማር ለወጪ ገበያ ለማቅረብ እየሠራ እንደሚገኝ የወናጎ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።

በወረዳው በማህበር ተደራጅተው በንብ ማነብ ሥራ የተሰማሩ ማር አምራች ማህበራት በዘርፉ ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የወናጎ ወረዳ በመሬት ጥግግት ምክንያት በ12 ሺህ ሄክታር መሬት ወደ 160 ሺህ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በዚህም ምክንያት ኦፍ ፋርም አክቲቪቲ ወይም በትንሽ ቦታ ተሠርቶ ገቢ የሚያስገኙ የግብርና ሥራዎች በተለይም የንብ ማነብ ሥራ በስፋት እንደሚሠራ ከወረዳው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በወረዳው በንብ ማነብ ሥራ ከተሰማሩ ማህበራት መካከል ሰላም የንብ ማነብ ማህበር አስር አባላትን ይዞ በዓመት ሁለት ጊዜ እስከ 160 ኪ.ግ ማር እንደሚያመርቱ የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ዳዊት ገልቹ ተናግሯል።

የማህበሩ አባላት የቁሳቁስና የክህሎት ግንዛቤ ድጋፍ ተደርጎላቸው ቢሠሩም የንብ ቀፎዎቹ ከጣራው ጋር ተያይዞ ያለው የሳር ኪዳን ለዝናብ የተጋለጠ በመሆኑ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

ኖጲኖ ሌላኛው አስር አባላት ያሉት የማር አምራች ማህበር እስከ 350 ኪ.ግ ማር እንደሚያገኙ የተናገረው ወጣት ታሪኩ ጀቦ የንብ ማነብ ሥራ በትንሽ ቦታ የሚሠራ ውጤታማ መስክ በመሆኑ ሌሎችም በዘርፉ እንዲሰማሩ ጠይቋል።

በወረዳው ከሚገኙ ማር አምራች አርሶ አደሮችና የወጣቶች ማህበራት ማር በመረከብ የሚሸጠው ስድሳ አባላት ያሉት የመሌቦ ማህበር የማር ሥራ አዋጭ ነው ተብለው ወደሥራ እንደገቡ የተናገረው የማህበሩ ሰብሳቢ ተስፋዬ ሽፈራ በየከተሞቹ የመሸጫ ስፍራ ከተመቻቸላቸው አስፍተው የመሥራትና ኦርጋኒክ ማር ወደ ውጪ ለመላክ ዕቅድ እንዳላቸው ተናግሯል።

በወረዳወ 2 ሺህ 646 ወጣቶችና 5 ሺህ 654 አርሶአደሮች በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተዋል ያሉት የወናጎ ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽ/ቤት የእንስሳትና አሳ ዘርፍ የንብና ሐር ልማት ባለሙያ አቶ ሳሙኤል ካሳሁን መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በክህሎትና በቁሳቁስ ድጋፍ እያደረጉ እንዳለ ተናግረዋል።

መንግስት በሌማት ትሩፋት መርሃግብር ሃያ 20 አርሶአደሮችን እያደራጁ በዘርፉ መሰመራታቸውን አቶ ካሳሁን አስረድተዋል።

የወናጎ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አበበ እጅጉ ሞይሽ የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት ወጣቶችን በማህበር አደራጅቶ በንብ ማነብ ሥራ ማሰማራቱን በመግለጽ የማር ምርት ከፍ እንዲል አድርጓል ብለዋል።

ማርን ወደውጭ ለመላክ በኦርጋኒክ ሰርተፊኬሽን ሂደት ላይ መሆኑን የተናገሩት አስተዳዳሪው ለዚሁ ዓላማ የሚሆኑ ማርን በስፋት የሚያመርቱ 1 ሺህ አርሶ አደሮች በመለየት እየተሠራ እንዳለ ገልጸዋል።

ከአንዳንድ ማህበራት የሚነሱ ለንብ ቀፎ የሚያገለግል የቆርቆሮ ጣሪያና የመሸጫ ቦታዎች ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠሩ እንዳለ አቶ አበበ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:  ውብሸት ካሳሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን