ሀዋሳ፡ ነሐሴ 20/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ሕገ ወጥ የጤና ግብዓቶች እና የምግብ ዝውውርን ለመከላከል ባለ ድርሻ አካላት ተቀናጅተው እንዲሠሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሐኒት ባለስልጣን ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤናና ጤና ነክ አገልግሎትና ግብዓት ጥራት ቁጥጥር ባለ ስልጣን ጋር በመሆን በህገ ወጥ መድሐኒት ንግድ እና ዝውውር ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በአርባ ምንጭ ውይይት በማካሔድ ላይ ነው።
በመድረኩ የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ እንዳሉት መንግሥት ባለፋት ዓመታት በዘረጋው የጤና ፖሊሲ መሠረት ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መጠን ከመቀነሱም በላይ የሞት ምጣኔ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ በክልሉ ሕገ ወጥ የመድሐኒትና ምግብ ዝውውር እየተበራከተ ይገኛል ያሉት አቶ እንዳሻው፥ በተደረገው የቅኝት እና ቁጥጥር ስራ 56 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ የመድሐኒት ዓይነቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አብራርተዋል።
ሕገ ወጥነትን ከመከላከል አኳያ ሕብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግም የቢሮ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሐኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሔራን ገርባ መድሐኒቶች እና ምግቦች በባለስልጣኑ ካልተመዘገቡ እና ጥራታቸው ካልተረጋገጠ ለጤና ጠንቅና ለሞት የሚያጋልጡ በመሆናቸው ለመከላከል ሁሉም የየራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
ከሰሐራ በታች ባሉ ሀገራት የሚስተዋለውን ሠላምና አለመረጋጋትን መነሻ በማድረግ የሕገ ወጥ መድሐኒት ዝውውር መበራከቱን የገለጹት ዳይሬክተሯ 126 ሚሊዮን 8 መቶ ሺህ ብር የሚገመቱ መድሐኒቶች እንዲወገዱ መደረጉንም ወ/ሪት ሔራን ገልጸዋል።
በሕገ ወጦች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተመጣጣኝ አለመሆኑና የባለ ድርሻ አካላት ትኩረት ማነስ ለሥራው አዳጋች እንደሆነም ተብራርቷል።
በውይይት መድረኩ የምክር ቤት አባላት፣ ሐይማኖት አባቶች፣ ከዞኖች እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ