የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል ሀገራት ኘሮጀክት አስተባባሪዎች እና የግብርና ሚንስቴር ብሔራዊ ኘሮጀክት ልዑክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን የድርቅ መቋቋሚያና ዘላቂ የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ኘሮጀክት የተሰሩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል ሀገራት ኘሮጀክት አስተባባሪዎች እና የግብርና ሚንስቴር ብሔራዊ ኘሮጀክት ልዑክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን የድርቅ መቋቋሚያና ዘላቂ የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ኘሮጀክት የተሰሩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ

ሀዋሳ፣ መስከረም 03/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል ሀገራት ኘሮጀክት አስተባባሪዎች እና የግብርና ሚንስቴር ብሔራዊ ኘሮጀክት ልዑክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን የድርቅ መቋቋሚያና ዘላቂ የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ኘሮጀክት የተሰሩ የልማት ሥራዎችን ጎበኝተዋል፡፡

የድርቅ መቋቋሚያና ዘላቂ የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ኘሮጀክት የአርብቶ አደር የምግብና ስርዓተ ምግብ ደህንነት /BREFONS/ ፕሮጀክት ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸውን በበናፀማይ ወረዳ የስቲንባ ቀበሌ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት  የእንጨቴ መኖ ልማትና የእንስሳት መኖ ባንክ የመስክ ምልከታ ተደርጓል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ለ4 ቀናት ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ከ8 ኢጋድ አባል ሀገራት መካከል ከ7ቱ ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ስታፍ ከዚህ ቀደም የድርቅ መቋቋሚያና ዘላቂ የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ኘሮጀክት (DRSLP)ና በአሁኑ ሰዓት የአርብቶ አደር የምግብና ስርዓተ ምግብ ደህንነት /BREFONS/ፕሮጀክት ባለፉት ዓመታት በደቡብ  ኦሞ ዞን በናፀማይ ወረዳ ያከናወናቸውን ተሞክሮዎችንና ያሉ ውስንነቶችን ለማረምና የፕሮጀክቱን ሂዲት ለማስቀጠል ያለመ የልምድ ልውውጥና የመስክ ምልከታ መሆኑም ተመልክቷል ።

የኢጋድ አባል ሀገራት አስተባባሪዎችን ወደ ወረዳቸው ስድረሱ አቀባበል ያደረጉት የበናፀማይ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ጋርሾ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ኘሮጀክቱ በወረዳው በተለያዩ ቀበሌዎች ያከናወናቸው የመጠጥ ውሃና ሌሎች ድርቅን ለመቋቋም የተሰሩ ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ መሆናቸውን አንስተው ለፕሮጀክቱ መሳካት የበኩላቸውን ሚና ለተወጡ የፌዴራል ፣ ክልልና ዞን ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።

የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ በበኩላቸው የደቡብ ኦሞ ዞን የበርካታ እምቅ ሀብት ባለቤት ናት ብለው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በአርብቶ አደሩ እንስሳት ላይ የሚደረሰውን የድርቅ አደጋዎችን ለመከለከል የመኖ ልማት ሥራዎችንና የእንስሳት ጤና ለመጠበቅ እንዲሁም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥራት ዞኑ ከፕሮጀክቶቹ ጋር በቅርበት ይሰራል ብለዋል።

በፌዴራል የኘሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጀማል አልዬ ኘሮጀክቱ በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች 59 የመጠጥ ውሃ ጉድጓዶችና ከ100 በላይ ምንጮችን የማጎልበትና በግጦሽ ልማት በምግብ እራስን መቻል በተፈጥሮ ሃብት አጠበበቅ የእንስሳት ጤና መጠበቅና ድርቅን መከላከል ላይ በርካታ ተግባራት ማከናወናቸውን ጠቁመው በቀጣይም በሁሉ ዘርፎች ተመሳሳይ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አከባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤካል ነትር ባደረጉት ገለጻ በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ አካባቢ በእንስሳት ምርታማነት ፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ፣ በኑሮ ዘይቤ ማሻሻያ ዙሪያ የክልሉ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢጋድ የክፍለ አህጉራዊ ዳይሬክተር አቶ ሙባሪክ ማቦያ እንደተናገሩት የጉብኝቱ ዓላማ በሪፖርት ሲላኩ የነበሩ ጉዳዮች በተጨባጭ መሬት ላይ መኖራቸውን ለማረጋገጥና በአባል ሀገራቱ መካከል የልምድ ልውውጥ በማድረግ ቀጠናዊ ዕድገቱንና ትስስሩን ለማጠናከር መሆኑን ጠቁመው በኢትዮጵያ ውስጥ ባደረጉት መስክ ምልከታው ፕሮጀክቶቹ እያከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆኑን ተናግረዋል ።

የወረዳው አርብቶአደሮች በበኩላቸው በባለፉት አመታት በአከባቢው በተፈጠረው ድርቅ የኑሮአቸው መሠረት የሆኑ እንስሳትን በሞት በማጣታቸው ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊና ስነልቦናዊ ቀውስ መዳረጋቸውን ገልጸው ኘሮጀክቱ ባደረገው ድጋፍ  በመኖ ልማትና በእንሰሳት ጤና እንዲሁም በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የተሻለ ለውጥ ማምጣት መቻላቸውን ተናግረዋል ።

ዘጋቢ : ጄታ ታገሠ -ከጂንካ ጣቢያችን