የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንደኛ ዓመት የምስረታ በዓል በደማቅ ስነ-ስርዓት እየተከበረ ነው

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 20/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንደኛ ዓመት የምስረታ በዓል በወላይታ ሶዶ ከተማ በደማቅ ስነ-ስርዓት በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡

ክልሉን የሰላም የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ላለፈው አንድ ዓመት ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ፈተናዎች ቢኖሩም የክልሉን ህዝቦች አብሮነትና መቻቻል አጠናክሮ ማስቀጠል ተችሏል ብለዋል።

ለዚህም የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች ላቅ ያለ ሚና እንደነበራቸው ርዕሰ መስተዳድሩ አንስተዋል።

ክልሉን ያጋጠሙ የተፈጥሮ አደጋዎችን ተከትሎ መላው ኢትዮጵያዊያን የአደጋ ሰለባዎችን በማፅናናትና በመደገፍ ረገድ ለተደረገው ርብርብ አቶ ጥላሁን አመስግነዋል።

የክልሉን የመልካም አስተዳደርና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት የጋራ ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ በቀጣይ የህዝብ ጥያቄን በመመለስ ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ::

ዘጋቢ፡ ሲሳይ ደበበ