በሲቪል ሰርቫንቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ግድፈቶች እንዲታረሙና ሌብነትን የሚፀየፍ ዜጋ ለመገንባት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 18/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሲቪል ሰርቫንቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ግድፈቶች እንዲታረሙና ሌብነትን የሚፀየፍ ዜጋ ለመገንባት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የፌደራልና የክልል ምክር ቤት ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከመራጩ ህዝብ ጋር ለአንድ ሳምንት ሲያካሄዱ የነበረው የማጠቃለያ መድረክ በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ተካሂዷል።

የፌደራልና የክልል ምክር ቤት ህዝብ ተወካዮች ከመራጩ ህዝብ ጋር በዓመት ሁለት ጊዜ ውይይት ያደርጋሉ።

የማጠቃለያ ውይይት መድረኩን የመሩት የፌደራል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶክተር ታደለ ቡራቃ በጠምባሮ ልዩ ወረዳ በየደረጃው በሚገኙ የህዝብ መድረኮች የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተነስተው ሰፊ ውይይት በማድረግ ባለቤት እንዲያገኙና በአመራሩ በኩል ልዩ ትኩረት እንዲሰጥባቸው አቅጠጫ ያስቀመጠ የማጠቃለያ መድረክ ስለመሆኑ ገልፀዋል።

በየደረጃው በተካሄደባቸው ልዩ ወረዳው፣ ክልልና የፌደራል መንግስት የሚፈታባቸው የህዝብ ጥያቄዎች መለየታቸውንም ዶክተር ታደለ ተናግረዋል።

በሲቪል ሰርቫንቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ግድፈቶች በተለይም በደመወዝ አከፋፈልና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ የአመለካከትና የተግባር ጉድለቶች እንዲታረሙና ሌብነትን የሚፀየፍ ዜጋ ለመገንባት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ልሰራ እንደሚገባም ዶክተር ታደለ አመላክተዋል።

የክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ወይዘሮ አሰለፈች ኃይሌ በበኩላቸው ላለፉት ሳምንታት ከህዝብ ጋር የተደረጉ መድረኮች የሚስተዋሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችን በማረም ህዝብና መንግስት ይበልጥ እንዲቀራረብ አጋዥ መድረክ መሆኑን ገልፀዋል።

በማህበራዊ ዘርፍ በተለይም በትምህርት ልማት ዘርፍ ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራና የዘርፉ ባለሙያዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለተሻለ ውጤታማነት እንዲሰራ አቋም የተያዘ መድረክ እንደሆነም ገልፀዋል።

የዝውውር፣ የቅጥር፣ የደረጃ እድገት፣ የመማሪያ መጽሐፍት እጥረትና የትምህርት አመራሩ የቅንጅት ጉድለት ችግሮች ልታረሙ እንደሚገባም በማጠቃለያው ውይይት ወቅት ተነስቷል።

የሙዱላ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ልዩ ወረዳው ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠቁሟል።

በውሃ፣ በመንገድ፣ በመብራትና በፍትህ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮች እንዲቀረፉና ህዝብ የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኝ አመራሩና ባለሙያው ከአድሎ የፀዳ አገልግሎት ለማስፈን የድርሻውን እንዲወጣ የህዝብ ተወካዮቹ አሳስበዋል።

በውይይቱ የልዩ ወረዳውና የሙዱላ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና ቋሚቴ አባላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ: ጡሚሶ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን