ሀዋሳ፡ ነሐሴ 18/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ ከብሪጅ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ድርጅት ጋር በትራንስፖርት ዘርፍ በዲጂታል ኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረሙ።
በውል ስምምነቱ ወቅት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትልና የክልሉ የመሠረተ ልማት ክላስተር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አማን ኑረዲን እንደገለፁት በትራንስፖርት ዘርፍ ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ የዲጂታል ኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ከዚህ ቀደም በወልቂጤና በሆሳዕና መናኸሪያዎች የሙከራ ትግበራ ሲከናወን ቆይቷል።
አሁን ላይ አገልግሎቱን በክልሉ በ7 መናኸሪያዎች ወደ ሙሉ ትግበራ ለመግባት የሚያስችል የውል ስምምነት ከብሪጅ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ድርጅት ጋር መፈጸሙን ነው የገለፁት።
ቴክኖሎጂው በተለይም በትራንስፖርት ዘርፍ በስፋት የሚስተዋለውን ትርፍ መጫንና ከታሪፍ በላይ ማስከፈልን እንደሚያስቀር አቶ አማን ተናግረዋል።
የቢሮው ምክትልና የትራንስፖርት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሰንበቶ አባባ በበኩላቸው ማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ከትራንስፖርት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ተከትሎ በዘርፉ በተለይም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት መስጠት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል ።
የብሪጅ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ክሪስቲያን ተሾመ እንዳሉት ድርጅታቸው የተለያዩ የሶፍት ዌር ውጤቶችን ለመንግስት እና ለግል ተቋማት እንደሚያቀርብ በመጥቀስ በተለይም በዘመናዊ የመናኸሪያ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ላይ የበለፀገ የዲጂታል ኢ-ትኬቲንግ ሶፍትዌር በሀገሪቱ በሚገኙ 56 መናኸሪያዎች ተግባራዊ መደረጉንና ከ450 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ተግባራዊ ለማድረግ ከስምምነት መደረሱንና ቴክኖሎጂው ለማህበረሰቡ ፈጣንና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት ዕድል እንደሚፈጥር በመግለፅ ስራው በገቡት ውል መሠረት ለመፈጸም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
በክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮና በብሪጅ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ድርጅት መካከል የተፈጸመው የውል ስምምነት ለሁለት ዓመት እንደሚቆይ ተገልጿል።
ዘጋቢ፣ መሃመድ ሽሁር- ከወልቂጤ
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ