ሀዋሳ፡ ነሐሴ 18/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኦሞ ዞን የኦሞ ወንዝና የቱርካና(ሩደልፍ) ሐይቅ ሞልቶ በኦሞራቴ ከተማና አካባቢው ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል
የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ የአደጋ መከላከልና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ አቶ አደፍርስ አሰፋ እንደገለፁት በአሁን ወቅት ወንዙ የማፈናቀል አደጋ አለማድረሱን ጠቅሰው ይሁንና ከኦሞራቴ ከተማ በስተቀኝ ከ1 ኪሎ ሜትር በማይበልጥ ርቀት ላይ ይገኛል ብለዋል።
በተቃራኒው በስተግራ ደግሞ የቱርካና ወይም የሩደልፍ ሀይቅ ሞልቶ ሜዳ ላይ በመፍሰስ በተመሳሳይ በቅርብ ርቀት ላይ እየተስፋፋ እንደሚገኝ ያብራራቱ አቶ አደፍርስ የውሃው መጠን ከቀን ወደቀን እየጨመረ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ለከተማውና ለአካባቢው ነዋሪዎች ግንዛቤ ከመስጠት በሻገር ወንዙ ወደ ከተማው ጥሶ እንዳይገባ ርብርብ እየተደረገ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ የወንዙ ፍሰት ከመጠን በላይ በመሆኑ የመከላከል ሥራውን አዳጋች አድርጎታል ብለዋል።
በአሁን ወቅት ሁኔታው እጅግ በጣም አሳሳቢ መሆኑን ነው ዋና አስተዳዳሪው የተናገሩት።
ለክልል፣ ፌዴራል እና ለሚመለከታቸው አካላት መረጃ መተላለፉንም አስታውቀዋል።
የዳሰነች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አቶ ታደለ ሐቴ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር በኩል የውሃ መጠኑን መቀነስ የሚያስችል መቀልበሻ መስመር ግንባታ የተሰራ ቢሆንም ውሃው በመስመሩ እየሄደ አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የጂንካ ቅርንጫፍ በአካባቢው የተለያዩ ሰብዓዊ ሥራዎችን እያከና እንደሚገኝ የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ቢሻው ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ- ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ፈጣንና ቀልጣፋ መረጃን ተጀራሽ በማድረግ የመንግስትና የማህበረሰቡን ተግባቦት ይበልጥ ለማጠናከር የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሚና የጎላ መሆኑ ተጠቆመ
ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው
በ17 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የሞሪንጋ ጂን ባንክ ለማቋቋም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ