ሀዋሳ፡ ነሐሴ 17/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የሚተከሉ ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው የጎላ በመሆኑ ትኩረት መሰጠቱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለፀ፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ ስለመሆኑ ተመላክቷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ስሩር በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ ባሰሙት ንግግር በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተከሉ ያሉ ችግኞች ለምግብነት፣ ለአከባቢ ጥበቃ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመዋል።
ባለፉት አመታት በክልል ደረጃ በርካታ ችግኝ መተከሉን የጠቀሱት አቶ ኡስማን በዚህ የሚታይ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው፥ የተተከሉ ችግኞች የመፅደቅ ምጣኔም እያደገ መጥቷል ብለዋል።
የብዝሃ እጽዋት ቁጥር ማደግ፣ የአፈር ለምነትና የምርትና ምርታማነት መጨመር፣ የአከባቢ ስነ ውበት መስተካከል ያለፉት አምስት አመታት ስራ ውጤት መሆኑን አመላክተዋል።
ይሄን ተከትሎ በክልሉ ያሉ የመስኖ አውታሮች የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አቶ ኡስማን ጠቁመዋል::
ህብረተሰቡ ላደረገው የነቃ ተሳትፎ አቶ ኡስማን ምስጋና አቅርበዋል።
በተከላ መርሃ ግብሩ ላይ ያገኘናቸው ተሳታፊዎች ለደቡብ ሬዲዮ ቴሌቪዥን ድርጅት በሰጡት አስተያየት ለመጭው ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ ይሄ ትውልድ የራሱን ግዴታ መወጣት አለበት ብለዋል።
የተተከሉ ችግኞች ፀድቀው ለፈላጊውን ውጤት እንዲያመጡ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡ ጀማል የሱፍ
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ