ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የበኩሉን ችግኝ አፍልቶ ማበርከቱን የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ገለፀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 17/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የበኩሉን ችግኝ አፍልቶ ለተከላ ማበርከቱን የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ አስታወቀ፡፡

የኮሌጁ ሠራተኞች የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈው የበኩላቸውን አሻራ ማሳረፋቸው ተጠቁሟል፡፡

የኮሌጁ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንተርኘራይዝ ምክትል ዲን መ/ር ጥላሁን አለማየሁ እንደተናገሩት ኮሌጁ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ታሳቢ በማድረግ ረጅም ጊዜ በመውሰድ ችግኝ ሲያዘጋጅ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ የሚውሉ ቡና 400 ሺህ በላይ፣ ሌሎች የደን ችግኞች እንደ ግራቢሊያና ሳሳ ያሉት ከ100 ሺህ ችግኞች ተዘጋጅተው ለተለያዩ ተቋማት መከፋፈሉን ገልፀዋል፡፡

በነሐሴ 17/2016 ዓ/ም እየተከናወነ ለሚገኘው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ 40 ሺህ ችግኝ መውሰዱን መ/ር ጥላሁን ገልፀዋል፡፡

እንደ ሀገር በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዬን ችግኝ ለመትከል እየተደረገ ያለውን እርብርብ ለማሳካት የኮሌጁ ሠራተኞች በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ሚሊኒየም ትምህርት ቤት በመገኘት ችግኞችን መትከላቸውን አብራርተዋል፡፡

የኮሌጁ አስተደደር ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዲን አቶ ግርማ ለገሠ በበኩላቸው ኮሌጁ ሀገሪቱ የአረንጓዴ አሻራ መተግበር ከጀመረችበት እስካሁን ባለው ጊዜ በቁጥር 500 ሺህ በላይ ችግኞችን አዘጋጅቶ በነፃና በግዥ ለአካባቢ ማህበረሰብ ሲያቀርብ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የተተከሉ ችግኞች ፀድቀው ውጤታማ መሆናቸውን አቶ ግርማ ጠቁመው ገና በመተከል ላይ ያሉት ችግኞች የተፈለገውን ዓላማ እስኪያሳኩ ድረስ ኮሌጁ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤን ለአካባቢው ማህበረሰብ ያስተምራል ብለዋል፡፡

የሚሊኒየም ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር፣ መምህር ሻንቆ ብርሃኑ እንዳሉት የኮሌጁ ማህበረሰብ የተከላቸው ቡና ችግኞች ለትምህርት ቤት ውስጥ ገቢ ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ ስለሆነ የመንከባከቡን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ – ከሚዛን ጣቢያችን