ከዛሬ ጀምሮ ለ2017 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ መጀመሩን የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ



መምሪያው በ2016 በክረምት ወቅት የተከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች አፈፃፀም ግምገማና የ2017 የተማሪዎች ቅበላ በተመለከተ በወልቂጤ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት ባለፉት ሁለት የክረምት ወራት በዞኑ በሚገኙ በሁሉም የትምህረት እርከኖች በቀጣይ በትምህርት ስራዉ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

ትምህርት ቤቶች የውስጥ ገቢያቸውን ማሳደግ እንዲችሉ ባላቸው ማሳ ላይ እንዲያለሙ መደረጉንም ገልፀዋል፡፡

አክለውም የመማሪያ ክፍሎችን ከመገንባትና ከመጠገን ረገድም የተሻሉ ስራዎች ተከናውኗል ብለዋል።

በ2017 የትምህርት ዘመን በዞኑ ውጤት ማስመዘገብ እንዲቻልም በቂ የቅስቀሳና የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ሀላፊው በዚህም ከ234 ሺ በላይ ተማሪዎች ከዛሬ ጀምሮ ምዝገባ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን አስተዳደር ረዳት የመንግስት ተጠሪ ወ/ሮ አመተሩፍ ሁሴን በበኩላቸው የትምህርት ስራ ሀገርን መገንባት የሚችል ትውልድ የሚቀረፅበት መሆኑን ተከትሎ በዘርፍ ውጤታማ ለመሆን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ስሜነሽ ግርማና አቶ ሽኩረታ አብድልከሪም በሰጡት አስተያየት በክረምቱ ወቅት ተማሪዎች ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ ትምህርት እንዲያገኙ ሲደረግ መቆየቱን ገልፀዋል።

በቀጣይ የመማር ማስተማሩን ሂደት ምቹ ለማድረግ ህብረተሰቡና የትምህርት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፍ ስራ እንደሚሰራም አብራርተዋል።

በመድረኩም የጉራጌ ዞን ቀይ መስቀል ማህበር የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት ችግር ላለባቸው ተማሪዎች የሚሆን ስድስት ሺህ ደብተሮችን ያበረከተ ሲሆን ይህም በገንዘብ ሲተመን ከ284 ሺ ብር በላይ መሆኑን አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡ ፉአድ አብደላ – ከወልቂጤ ጣቢያችን