ሀዋሳ፡ ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በባስኬቶ ዞን በላስካ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የመድኃኒት እጥረትና የተኝቶ መታከሚያ ክፍል ችግሮች እንዲቀረፉ የሆስፒታሉ ተገልጋዮች ጠየቁ።
አስተያየታቸውን የሰጡ ተገልጋዮች እንዳሉት በሆስፒታሉ የመድኃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ ከግለሰብ የመድኃኒት መሸጫ መደብሮች በውድ ዋጋ ለመግዛት ተገደናል፡፡
ሲስተር ትብቃሽ ቱሉ በሆስፒታሉ የህፃናት ሀኪም ስትሆን በተመጣጠነ የምግብ እጥረት የተጎዱ ህፃናት ህክምና በስፋት እየተሰጠ ሲሆን ይህንም አገልግሎት ተደራሽና ቀልጣፋ ከማድረግ አኳያ ውስንነቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በነፃ የገንዘብ ድጋፍ (ፈንድ) ይመጡ የነበሩ መድኃኒቶች መቋረጥ በሆስፒታሉ በቂ የመድኃኒት አቅርቦትና የተኝቶ ታካሚ መኝታ ቦታ አለመኖሩ በህክምናው ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን በመግለፅ እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የሚመለከታቸው አካላት በቅርበት እንዲሰሩ ሲስተር ትብቃሽ ጠይቀዋል።
በሆስፒታሉ የተኝቶ ክፍል አስተባባሪ አቶ ማስተዋል ይኼይስ በሆስፒታሉ የሰው ኃይል እጥረት ቢኖርም አገልግሎቱን ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ ባሉ ባለሙያዎች ሁሉም አይነት ህክምናዎች እየተሰጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የላስካ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ፀጋዬ ላቀው ሆስፒታሉ ለሰፊ የህብረተሰብ ክፍል አገልግሎት ስለሚሰጥ የተለያዩ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ገልፀው በቂ የሰው ሃይል አለመኖር፣ የመድኃኒት አቅርቦት፣ የተኝቶ መታከሚያ የክፍል እጥረትና የባለሙያ የትርፍ ሰዓት ክፍያ ችግሮች እንዳሉ ገልጸዋል።
ችግሮቹን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ከዞን አስተዳደር እና አርባምንጭ ከሚገኘው ከኤፕሳ የመድኃኒት መሸጫ ጋር በመነጋገር መድኃኒት በብድር እንዲቀርብ እና የባለሙያ እጥረትን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፥ የተበላሹ ማሽኖችን በማስጠገን ስራ መጀመሩን የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ሲስተር መዓዛ ፍሬው ገልጸዋል።
ከባለሙያ የትርፍ ሰዓት ክፍያና ከተኝቶ መታከሚያ ክፍል ጋር ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከዞን አስተዳደር ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ዓቢይ ይኼይስ – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ