ሀዋሳ፡ ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሞዴል አርሶ አደሮችን በማሳተፍ የቡና መንደር ምስረታና የማስተዋወቅ ስራን በተለያዩ አካባቢዎች እያከናወነ መሆኑን የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡
ማዕከሉ ከቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በቂጤ ቀበሌ ሞዴል አርሶአደሮች የቡና መንደር ምስረታና የማስተዋወቅ ፕሮግራም አካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙ አርሶ አደሮች ቡናን ሳይንሳዊ መንገድን ተከትሎ በመትከልና በመንከባከብ ውጤታማ ለመሆን እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተወካይና የመነሻ ቴክኖሎጂ ብዜትና ዘር ምርምር ዳይሬክተር አቶ ታምራት ገብሬ፤ ቡናን በስፋትና በጥራት ለማምረት በክልል ደረጃ ንቅናቄ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው በምርምር የተለዩትን መትከል ላይ ትኩረት እንደተሰጠው ጠቁመዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ማናጀር ዶክተር አብይ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው ክልሉ ቡናና ቅመማቅመም የሚመረትበት መሆኑን ተናግረው ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠል በምርምር የታገዘ ስራ ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል።
አሁን ላይ የክልሉ የቡና ሽፋን 560 ሺህ ሄክታር መድረሱን ተናግረዋል፡፡
7 ሺህ 454 የቡና ዝርያዎች ከሌሎች በሽታን የመከላከል አቅሙ፣ ምርት መስጠት፣ አካባቢን በመላመድ የተሻለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቦንጋ ግብርና ምርምር ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ማረኝ ዓለሙ ናቸዉ፡፡
የቡና መንደር ምስረታና የማስተዋወቅ ስራ በክልሉ ቤንች ሸኮና ካፋ ዞኖች 2 ወረዳዎች ደቡብ ቤንችና ቢጣ ወረዳ በ15 ሄክታር መሬት ላይ የሚከናወን መሆኑን የገለጹት አቶ ማረኝ፤ በሌሎችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ኪዳኔ ሸቅ በወረዳው ካሉ 24 ቀበሌዎች 16ቱ ቡና እንደሚያመርቱ አንስተዋል፡፡
በሞዴል አርሶ አደር ደረጃ ቡና በሄክታር እስከ 12 ኩንታል እንደሚገኝ ገልጸው በ2015 ዓመተ ምህረት 15 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ተልኳል ብለዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ሞዴል አርሶ አደሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የስራ ሀላፊዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ብዙአየሁ ጫካ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ