ሀዋሳ፡ ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተጠናቀቀው 2016 በጀት አመት 302 የትራፊክ አደጋዎች መከሰታቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በክልሉ ካሉ 22 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት መካከል 15ቱ ከደረጃ በታች በመሆናቸው እርምጃ መውሰዱንም ቢሮው አስታውቋል፡፡
በተጠናቀቀው 2016 በጀት አመት 302 የትራፊክ አደጋዎች የተከሰቱ ሲሆን 611 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት ሲደርስ 71 ሰዎች ደግሞ ለሞት መዳረጋቸውን የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊና የትራንስፖርት ዘርፍ ሃላፊው አቶ አሸብር ኢካሎ ተናግረዋል።
በየጊዜው ለሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች መንስኤ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስና ህጋዊነት ተጠቃሽ ምክንያት ናቸው ብለዋል።
በክልሉ 22 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ያሉ ሲሆን ከእነዚህም 15 የሚሆኑት መስፈርቶችን ያላሟሉና ከደረጃ በታች በመሆናቸው ለ4 ወራት እገዳ ተጥሎባቸዋል ነው ያሉት።
በደረሰው የትራፊክ አደጋ ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ የንብረት ውድመት ማስከተሉን የተናገሩት አቶ አሸብር 77 የሚደርሱት አደጋዎች የደረሱት ያለመንጃ ፍቃድ ሲያሽከረክሩ በነበሩ አሽከርካሪዎች መሆኑን ገልጸዋል።
በፍጥነት ማሽከርከር፣ ለእግረኛ ቅድሚያ ያለመስጠትና ያለመንጃ ፍቃድ ማሽከርከር ዋነኛ የትራፊክ አደጋዎች ምክንያት መሆናቸውን አቶ አሸብር ጠቁመዋል።
በተለይ በአሽከርካሪ ማስልጠኛ ተቋማት ያሉ ህገወጥ አሰራሮችን ለማረም በሚደረገው ጥረት በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራሮችና ሃላፊዎች የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ