ሀዋሳ፡ ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የፍጆታ ዕቃ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን በኮሬ ዞን የኬሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
የከተማው አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት በበኩሉ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ከ50 በላይ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን ተናግሯል።
ካነጋግርናቸው የኬሌ ከተማ ነዋሪዎች ወ/ሮ ፈለቀች ወዬሳ እና ሃይማኖት ኪዳኔ ከዚህ ቀደም እህል በሚሰበሰብበት ወቅት በተመጣጣኝ ዋጋ ይሸምቱ እንደነበርና ዘንድሮ ግን የእህል ዋጋ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፥ ከፋብሪካ ምርቶች ዘይትና ስኳር ዋጋቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በከተማው ህጋዊ ፍቃድ ካላቸው የእህል ነጋዴዎች አቶ ጦረኛ ሉፉዋዴ እና ተመስገን ሳፊሳ ህጋዊ ፍቃድ የሌላቸው ደላሎች የእህል ገበያ መረጋጋት እንዳይኖር አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠራቸውን ገልጸው፥ የፋብሪካ ውጤቶችን ከሚያቀርቡ ነጋዴዎች ወ/ሮ አለምነሽ አለማየሁ በበኩላቸው፥ ዘይትና ስኳር የጨመረው ከቦታው ዋጋ ከመጨመሩ በላይ፥ የትራንስፖርት ሁኔታ ምቹ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚያወጡት ወጪ በመናሩ መሆኑን አብራርተዋል።
የከተማው ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ንግድ ኢንስፔክሽንና ገበያ ልማት ሬጉሌሸን ዳይሬክቶሬት አቶ ባህሩ ባጃ ገበያን ለማረጋጋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅተው እየሠሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኬሌ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮርዳኖስ ጭርዶ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ከ50 በላይ ነጋዴዎች ላይ ሱቃቸውን ከማሸግ አንስቶ በማሠር ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
በዋናነት ህገወጥ ደላሎችን ከግብይት ሥርአት እንዳይከላከሉ የህጋዊ ነጋዴዎች ሽርክና መኖሩን የተናገሩት አቶ ዮርዳኖስ የተረጋጋ ግብይት ስርአት በዘላቂነት እንዲኖር ከገበያ አረጋጊ ግብረ ኃይሎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስታውሰዋል።
ዘጋቢ፡ ምርጫ መላኩ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
በትምህርት ሴክተር የመረጃ አያያዝ ውጤታማነት ዙሪያ በኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በትምህርታቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋና ቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ