ዲግሪና ከዚያ በላይ ያሉ የትምህርት ማስረጃዎችን ህጋዊነት ለማጣራት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ዲግሪና ከዚያ በላይ ያሉ የትምህርት ማስረጃዎችን ህጋዊነት ለማጣራት 83 ሺህ 68 የትምህርት ማስረጃ መሰብሰብ መቻሉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀምና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ መድረክ በዲላ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል፡፡

የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በመክፈቻ ንግግራቸው የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በተደረገው ርብርብ አበረታች ውጤት መታየቱን ጠቁመው፥ 6 ሺህ 766  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት 5 ሺህ 704 ችግሮች መፈታታቸውን ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ማስረጃዎችን ህጋዊነት ለማጣራት ምዝገባ ለማድረግ ከታቀደው 90 ሺህ 124 ድግሪና ከዚያ በላይ ደረጃዎች 83 ሺህ 68 የትምህርት ማስረጃ መሰብሰብ እንደተቻለና በቀጣይ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም አቶ ንጋቱ አስረድተዋል፡፡

ብልሹና ህገወጥ አሠራሮችን ለመከላከል ከቅጥርና ደረጃ ዕድገት ጋር በተያያዘ 30 ሺህ 910 የትምህርት ማስረጃ ፋይሎች በመመርመር 3 ሺህ 229 ፋይሎች ህገወጥ መሆናቸው ተረጋግጦ የማስተካከያ እርምጃ መውሰዳቸውንም ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

በዚህም ሊባክን የነበረው 1መቶ 10 ሚሊዮን 493 ሺህ በላይ ገንዘብ ማዳን እንደተቻለና ካለፉት ዓመታት ጀምሮ የባከነ 13 ሚሊዮን 45 ሺህ ብር በላይ ወደ መንግሥት ካዝና የማስመለስ ሥራ መሠራቱን ገልፀዋል፡፡

በመድረኩ በ2016 በጀት ዓመት ከ12 የዞን መምሪያዎችና ዩኒቶች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተቋማት ዕውቅናና ሽልማት ለመስጠት የተዘጋጀ መድረክ ነው ተብሏል፡፡

ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን