በጤና ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ የእናቶችና የህጻናት ሞት ለመቀነስ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የዲላ ዙሪያ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
ጽ/ቤቱ የተቋሙን የ2016 ዓ.ም አፈጻጸምና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ገምግሟል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታርኩ ታደሰ በጤና ዘርፍ የተቀመጡ ዋና ዋና ግቦችን ለመፈፀም በተደረገው ርብርብ ጥሩ አፈፃፀም መመዘገቡን ጠቅሰው፥ አንድም እናት በወሊድ ምክንያት መሞት የለባትም በሚል መርህ ሲሰራ እንደነበር አስታውሰው፥ ቤት መውለድን ተከትሎ የሚመጡ ችግሮችን ለማስቀረት በቅንጅትና በንቅናቄ እየሠሩ መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ማህበረሰብ አቀፍ የጤና አገለግሎት በማጠናከር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ በተከናወኑ ተግባራት የተመዘገበው ውጤት ዘላቂነት እንዲኖረው፥ የህክምና ተቋማት ለተገልጋዮች ጽዱና ውብ ለማድረግ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የወረዳው ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበባየሁ ማርቆስ በበኩላቸው፥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ፣ ተላላፊ በሽታዎች በመከላከልና በሌሎች ዘርፎች የታየውን መልካም ተሞክሮዎችን በማስቀጠል የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
በአከባቢው ከፍተኛ የወሊድ ምጣኔ ያለበት በመሆኑ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ኃላፊው በመድረኩ የተሻለ የፈጸሙትን በማበረታታት በአፈፃፀም ደከም ያሉትን ከሌሎች ተሞክሮ የሚወስዱበት መድረክ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ሩህሩህ ተንከባካቢና ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ባለሙያ በመፍጠር የህብረተሰቡን ፍላጎት ማሟላት እንደሚገባም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ሲስተር ብዙአየሁ መኮንንና አቶ ምህረቱ ደያሶ የኡዶና ወቻማ ጤና ጣቢያ ባለሙያዎችና የውይይቱ ተሳታፊዎች ሲሆኑ የበዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን በመጠቆም ከሎጂስትክ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በቅንጅትና በጥምረት መስራት እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ
አካባቢን በመጠበቅና በማጽዳት ምቹና ጽዱ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሁሉም የድርሻውን ልወጣ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳሰቡ
ግለሰባዊ ነጠላ ትርክቶችን በጋራ በመታገል በመደመር እሳቤ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ