በአንድ ጀንበር 2 ነጥብ 3 ሚሊዬን ችግኝ ለመትከል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአንድ ጀንበር 2 ነጥብ 3 ሚሊዬን ችግኝ ለመትከል አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የምእራብ ኦሞ ዞን ግብርና አከባቢ ጥበቃ ህብረት ስራ መምሪያ አስታወቀ።

በተከላው በ92 ቀበሌያት 23 የተከላ ቦታዎች መለየታቸውን እና 475 ሄክታር መሬት እንደሚሸፈን ተጠቁሟል።

በአርብቶ እና ከፊል አርሶ አደር ወረዳዎች የሚታወቀው የምእራብ ኦሞ ዞን ያለውን የደን ሽፋን ለማሳደግ በ2016 በጀት አመት 26 ሚሊዬን የተለያዩ የደን እና የፍራፍሬ ችግኞችን ለማዘጋጀት ግብ ተጥሎ ወደስራ መገባቱን የጠቆሙት የዞኑ ግብርናና ደን አከባቢ ጥበቃ ህብረት ስራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መልኬ ኬላጌ ናቸው።

ከእቅዱ 19 ነጥብ 2 ሚሊየን ችግኝ መዘጋጀቱን ጠቁመው፥ በዚህም በ768 ህዝብ ተሳትፎ 7ሺ 680 ሄክታር መሬት ለመሸፈን እየተሰራ ነው ብለዋል።

እስካሁን ባለውም 7 ነጥብ 2 ሚሊየን ችግኞች በ2ሺ 850 ሄክታር መሬት ላይ በ475 ሺ ተሳታፊ ህዝብ መተከል መቻሉንም ጠቁመዋል።

እንደ ሀገር በአንድ ጀንበር 600 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ከተያዘው እቅድ ውስጥ አንድ አካል የሆነው የምእራብ ኦሞ ዞን ባሉት ሰባት ወረዳዎች እና በሶስት የከተማ አስተዳደሮች 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ችግኝ በ475 ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በዞኑ የተለዩ 92 ቀበሌያት 23 ሳይቶች መኖራቸውን ገልጸው እነዚህ ሳይቶች ከፌደራል ጋር የተሳሰሩ በመሆናቸው በፌደራል ቋት ላይ የሚገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተከላውም 226 ሺ 8 መቶ የዞኑ ህዝብ ተሳታፊ እንደሚሆን የተናገሩት ኃላፊው በአሁኑ ሰአት ችግኞቹ ወደተከላ ስፍራዎች በመጓጓዝ ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በተከላውም ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ አርሶ እና አርብቶ አደሮች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ተናግረዋል።

ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን