ምክር ቤቶች የአስፈጻሚ አካላትን ተግባራት የመከታተልና ድጋፍ የማድረግ ሥራዎችን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተጠቆመ

ምክር ቤቶች የአስፈጻሚ አካላትን ተግባራት የመከታተልና ድጋፍ የማድረግ ሥራዎችን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተጠቆመ

የሸካ ዞን ምክር ቤት 5ኛ ዙር 11ኛ የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።

የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ዮሐንስ ካሳሁን በመክፈቻው ባደረጉት ንግግር ምክር ቤቱ የዞኑን የሴክተር መሥሪያ ቤቶች የሥራ እንቅስቃሴ ከመከታተልና ድጋፍ ከመስጠት ጋር ተያይዞ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ተናግረው በተለይም ከማህበራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በዞኑ የጤና ስጋት ሆኖ የዘለቀው የወባ በሽታ መከላከል ሥራና የመድሃኒት አቅርቦት ተግባራት ላይ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውንና በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከከተማ ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ የሚታዩትን ችግሮች በመቅረፍ በ2017 በጀት አመት የተሻለ የመሬት አቅርቦትን በማዘጋጀት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ አባል እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ በቀረበው የዞኑ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ በሠጡት አስተያየት እቅዶች ሲገመገሙ በተቀመጠላቸው ስታንዳርድ መሠረት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

ሌላው የምክር ቤቱ አባልና በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው ምክር ቤቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ አሠራሮቻቸውን እያሻሻሉ መምጣታቸውን ተናግረው የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በተሻለ መልኩ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ምክር ቤቱ በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ ለተከታታይ ሁለት ቀናት የሚመክር ሲሆን ከእነዚህም አጀንዳዎች መካከል የ2016 በጀት ዓመት የዞኑ ምክር ቤት፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የዞኑ አጠቃላይ አፈጻጸም ሪፖርት ማቅረብን ጨምሮ የ2017 ረቂቅ በጀት እንዲሁም የተለያዩ ሹመቶች ቀርበው የሚጸድቁ ስለመሆኑ ከወጣው ፕሮግራም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዘጋቢ፡ አስታወሰኝ በቃሉ – ከማሻ ጣቢያችን