የደብረታቦር በዓል በሆሳዕና ከተማ በድምቀት ተከበረ

የደብረታቦር በዓል በሆሳዕና ከተማ በድምቀት ተከበረ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደብረታቦር በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በሆሳዕና ደብረ -ምህረት ወደብረ-ታቦር ቅዱስ በዓለ-ወልድ ወቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል።

የሆሳዕና ደብረ ምህረት ወደብረታቦር ቅዱስ በዓለወልድ ወቅዱስ ገብርኤል ቤ/ያን አስተዳዳሪ መላከ ሰላም ቀሲስ ተዘራ ከበደ እና በሀዲያ ስልጤ ሀገረ ስብከት የሆሳዕና ካህናት ማሰልጠኛ ተቋም ርዕሰ መምህርና የሆሳዕና ደብረ ፀሐይ አቡነ ተክለሀይማኖት ቤ/ያን አስተዳዳሪ መጋቤ ሰናያት ቀሲስ ፍስሐ ሀብተወልድ የደብረ ታቦር በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ሶስቱን ደቀ መዛሙርት ይዞ ወደ ደብረ ታቦር ተራራ በመውጣት ግርማ መለኮቱን የገለጠበትን አብነት በማድረግ የሚከበር ታላቅ በዓል መሆኑን ገልፀዋል።

የደብረ ታቦር በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያን ከሚከበሩ ከ9ኙ አበይት በዓላት መካከል አንዱ መሆኑንም ተናግረዋል።

ደብረ ታቦር ቃሉ የግዕዝ ሲሆን ትርጉሙም የታቦር ተራራ ነው፡፡ በኢየሩሳሌም ናዝሬት አካባቢ በሰማሪያ አውራጃ የሚገኝ ተራራ ነው ያሉት አባቶቹ ኢየሱስ ክርስቶስ ሶስቱን ደቀ መዛሙርት፥ ጴጥሮስን ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ተራራው በመውጣት ግርማ መለኮቱን የገለጠበትን አቢነት በማድረግ የሚከበር ታላቅ በዓል ነው ብለዋል።

በዓሉ ሲከበር በተራራው ላይ የተከሰተው ታላቅ ነጎድጓድ ምሳሌ ጅራፍ ማጮህ፣ ለተገለጠው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ ችቦ ማብራትና እንዲሁም በወቅቱ ተዓምራት ተመስጠው በቦታው ላረፈዱ እረኞች ቤተሰቦቻቸው ለመብያ የሚሆን ምግብ ምሳሌ ሙልሙል ማዘጋጀት በበዓሉ ወቅት የሚከወኑ ሃይማኖታዊ ትውፊቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወቅቱ በሃይማኖቱ አስተምህሮ የክረምት ማብቅያ፣ ከጉምና ጭጋግ መላቀቂያ ወደ አዲሱ የፀደይ ዘመን መሻገሪያ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ዘጋቢ:-አማኑኤል አጤቦ- ከሆሳዕና ጣቢያችን