በድልድይ መሠረተ ልማት ችግር ምክንያት ለተለያየ እንግልት እየተዳረግን ነው ሲሉ በይርጋጨፌ ወረዳ የሀዳ-ቱሊሴ ቀበሌ ነዋሪዎች ተናገሩ

በድልድይ መሠረተ ልማት ችግር ምክንያት ለተለያየ እንግልት እየተዳረግን ነው ሲሉ በይርጋጨፌ ወረዳ የሀዳ-ቱሊሴ ቀበሌ ነዋሪዎች ተናገሩ

የክልሉ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ ድልድዩን ለመገንባት የሳይት ርክክብ አድርጎ ለግንባታው የዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አስታወቋል።

በወረዳው ከሚገኙ 26 ቀበሌያት አብዛኛዎቹን አቋርጦ የሚያልፈው ትልቁ የወጊዳ ወንዝ የሀዳ ቱሊሴ ማህበረሰብ ፈተና ከሆነ አመታት መቆጠራቸው ተመላክቷል፡፡

የአካባቢው ማህበረሰብ ወንዙ ላይ በእንጨት ርብራብ ይሠራው የነበረው ባሕላዊ ድልድይ ክረምት በመጣ ቁጥር በወንዙ ስለሚወሰድ መሻገር እንደማይችሉና ደፍረው የሚሻገሩ ካሉም ለሕይወት መጥፋት ካልሆነም ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አለማየሁ ሚጁና ጴጥሮስ አለሙ ተናግረዋል።

ወረዳውን ከሌሎች ወረዳዎችና አጎራባች ቀበሌያት ጋር የሚያገናኘው ይኸው ድልድይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት፣ ወላድና ታማሚ ወደ ጤና ተቋም፣ ነጋዴና አርሶአደሩም ወደገበያ ለመሄድ እየተቸገሩ እንዳለ ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ቃሲም ሁሴን አብራርተዋል።

የህብረተሰቡን ቅሬታ የሚጋሩት የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ሚጁ፤ በባህላዊ ዘዴ የተሠራው የእንጨት ድልድይ በክረምት ወንዝ ስለሚወስደው የህብረተሰቡ ግንኙነት እንደሚቋረጥ በመጥቀስ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችንም ማድረግ እንደማይቻል አስረድተዋል።

የድልድይ ግንባታው የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን የሠራው 46 ኪሎ ሜትር መንገድ አካል ቢሆንም በወቅቱ ሳይሠራ መቅረቱን ያስታወሱት አስተዳዳሪው ለክልሉ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን በተደጋጋሚ ጥያቄ በማቅረብ አሁን ከስምምነት መድረሳቸውን ገልጸዋል።

የሀዳ ቱሊሴን ወይም ወጊዳ ሁለት የድልድይ ግንባታ ለማከናወን የሳይት ርክክብ አድርገናል ያሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ዲላ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሐየሱስ ካሳዬ፤ ድልድዩ የሚያርፍበት ቦታና ስፋቱ ከተለመዱ የድልድይ አይነቶች ለየት ስለሚል፤ እንዲሁም አካባቢው ብዙ ምርት የሚወጣበት በመሆኑ ፍሰቱን የሚመጥን ጥናት መጠናቱን ተናግረዋል።

ለድልድዩ ግንባታ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በጨረታ ግዢ መጀመሩን የሚናገሩት ስራ አስኪያጁ ከአንድ አመት እስከ አንድ አመት ተኩል የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተሰርቶ እንደሚጠናቀቅ አስረድተዋል።

ዘጋቢ: ውብሸት ካሣሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን