የኣሪ ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ መቋረጥ የተለያዩ አካባቢያዊና ሀገራዊ መረጃዎችን እንዳንሰማ አድርጎናል ሲሉ በኣሪ ዞን በገሊላ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ አድማጮች ገለፁ

የኣሪ ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ መቋረጥ የተለያዩ አካባቢያዊና ሀገራዊ መረጃዎችን እንዳንሰማ አድርጎናል ሲሉ በኣሪ ዞን በገሊላ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ አድማጮች ገለፁ

አስተያየታቸውን ከሰጡን የከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ አብነት እያሱ፣ ማንደፍሮ ታንና ሌሎችም እንደገለፁት ሚዲያው በሁሉም ዘርፍ ወቅታዊና ትምህርታዊ የሆኑ አካባቢያዊና ሀገራዊ መረጃዎችን “የኣሪ አፍ” ቋንቋን ጨምሮ በአማርኛ ቋንቋ መረጃ በመስጠትና በማዝናናት ብሎም የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን በማጠናከር አይተኬ ሚና እንደነበረው ያነሳሉ።

አሰተያየት ሰጪዎቹ አክለውም ሚዲያው ማንነታችንን፣ ባህላችንን ብሎም ቋንቋችንን እንድናሳድግ ያስቻለ በመሆኑ ተሞክሮዎችን ለማስፋትና ሚዲያ አለምን አንድ መንደር የማድረግ አቅም ያለው በመሆኑ መፍትሔ ለመስጠት ወረዳውም ሆነ ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥተው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በወረዳው የኣሪ ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲሞክራሲ ደይሪ፤ ሬዲዮ ጣቢያው በወረዳው አሰተዳደር የበጀት ድጋፍና በማህበረሰቡ መዋጮ የሚተዳደር እንደመሆኑ በገጠመው “ዮኘኤስ” የተሰኘ መሳሪያ ብልሽት ምክንያት መቋረጡንና ወጪውም እስከ 4 መቶ ሺህ ብር በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ከወረዳው ጋር በመሆን የተለያዩ አካላትን ለማናገር ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰሜን ኣሪ ወረዳ ዋና አሰተዳዳሪና የሬዲዮ ጣቢያው ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ደግፌ ጌታቸው በበኩላቸው ሚዲያው ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበት የተከፈተ እንደመሆኑ የገጠመው የዕቃ ብልሽት ዋጋው ከፍ ያለ በመሆኑ በበጀት እጥረት ችግሩን ለመፍታት ዞኑንና ጂንካ ዮኒቨርስቲን ድጋፍ በመጠየቅ ለመፍታት ማቀዱን ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን