ጉዳዮች በከንቲባ ችሎት መታየታቸው የባለጉዳዩ ያልተገባ እንግልት የሚያስቀር መሆኑ ተገለፀ

ጉዳዮች በከንቲባ ችሎት መታየታቸው የባለጉዳዩ ያልተገባ እንግልት የሚያስቀር መሆኑ ተገለፀ

በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር እየተሰጠ ያለዉ የከንቲባ ችሎት አገልግሎት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመላክቷል፡፡

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው፤ ችሎቱ የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቅርበትና ግልፀኝነት በተሞላበት መልኩ በመፍታት ህዝብና መንግስትን የሚያቀራርብ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከንቲባው በማከልም ችሎቱ በባለጉዳዩ ዘንድ ለረጅም ጊዜ ያልተፈቱና በፍርድ ቤት ያልተያዙ ማንኛውም ጉዳይ ይዞ የሚቀርብበት በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ከማዘጋጃ ቤቱና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን መረጃ በማጣራት እንደየሁኔታው ፈጣንና ትክክለኛ ምላሽ የሚያገኝበት ነው ሲሉ ገልፀዋል።

ጉዳዮች በከንቲባ ችሎት መታየታቸው የባለጉዳዩን ያልተገባ እንግልት የሚያስቀር መሆኑን የተናገሩት ከንቲባዉ፤ በዚህም እየተሰጠ ያለዉ የችሎት አገልግሎት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል፡፡

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ይብጌታ ንጋ በበኩላቸው ችሎቱ ባለጉዳዩ ይዞት ከሚመጣው ጉዳይ አብዛኛው ከማዘጋጃ ቤት ጋር ተያያዥ መሆኑን አስታውሰው ይህም አስተዳደሩ በተቻለ አቅም እንደየክብደታቸዉ ቅደም ተከተል መሰረት መፍትሄ ለመስጠት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ንቅበሸዋ ችሎቱ በሃገሪቱ ባሉ ትልልቅ ከተሞች እየተተገበረ እንዳለ አውስተው ካለው ፋይዳ አኳያም ከነዚሁ ከተሞች ልምድ በመውሰድ የከንቲባ ችሎት እየተካሄደ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ፍርድ ቤቶች በብዛት የወንጀልና ፍትሃብሄር ነክ ጉዳዮች የሚታይገባቸዉ መሆኑን በመግለፅ ጉዳዮች ሁሉ በፍርድ ቤት ብቻ ተወስኖ የሚያልቅ ስለማይሆኑ ይህ ችሎት የፍርድ ቤቶች ጫናን የሚቀንስ መሆኑን ያወሱት ደግሞ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ታሪኩ ዳቢየ ናቸው።

በእለቱ የተገኙ ባለጉዳዮች በሰጡት አስተያየት የከንቲባ ችሎት ለረጅም ጊዜ ሳይፈቱ የቆዩ ጉዳዮቻቸውን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በጋራ መታየቱ እንዳስደሰታቸው ገልፀው ችሎቱ የባለጉዳዩን ያልተገባ እንግልት የሚያስቀር መሆኑንም ተናግረዋል።

የከንቲባ ችሎቱ በየሳምንቱ ሀሙስ የሚካሄድ ሲሆን ባለጉዳዩ በስራ ቀናት በከተማ አስተዳደሩ ፅህፈት ቤት በተዘጋጀው ቅሬታ ማቅረቢያ ፎርም ላይ ስለጉዳዩ የሚገልፅ አጭርና ግልፅ መረጃ በመሙላት ወረፋ ማስያዝና በቀጠሮ ዕለት ተዘጋጅቶ መገኘት እንደሚጠበቅበትም ተመላክቷል።

ዘጋቢ፡ በሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን