የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በክልሉ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ ይወሰዳል ሲል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለፀ።

ህብረተሰቡ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላት ሲያጋጥሙት ለሚመለከተው የንግድ አካል ጥቆማ በመስጠት የድርሻቸውን እንዲወጡም ቢሮው ጥሪውን አቅርቧል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ እንደተናገሩት መንግስት ከሰሞኑ በሀገሪቱ ያደረገው ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን ይህም የሀገሪቱን ጥቅል የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያረጋግጡ በርካታ ቱርፋቶች በውስጡ መያዙን አብራርተዋል።

ይሁን እንጂ ይህንኑ ወቅታዊ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራ ምክንያት በማድረግ በክልሉ በተለያዩ ከተሞች ላይ የሚገኙ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ እንዳሉም ተናግረዋል

አሁን ላይ እንደሀገር እየተከናወኑ ያለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ትልቅ ሀገራዊ ጠቀሜታ ያለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቢሆንም ህብረተሰቡን ባልተገባ መንገዶች በማደናገር ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ህገወጥ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እና መሰል ህገ ወጥ የንግድ ተግባራት ላይ እየተሳተፉ ባሉ ነጋዴዎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወስድ አቶ ተመስገን ገልጸዋል።

በተለይ መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ ቁጥጥር እየተደረገ የክልሉ መንግስት ሲሰራ መቆየቱን የተናገሩት አቶ ተመስገን ባልተገባ መልኩ ዕጥረት እንዲፈጠርና ምርትን በመደበቅ የንግድ አሻጥር እየሰሩ ባሉ ህገወጦች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራርና ባለሙያዎች እየታየ ያለውን ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በፍጥነት ለመቆጣጠር በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ህብረተሰቡ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ እነዚህን ህገወጦች ሲያስተውል ለሚመለከተው የንግድ አካል ጥቆማ በመስጠት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አቶ ተመስገን አሳስበዋል።

በቀጣይም በክልሉ ባሉ ዞኖች ላይ በሚገኙ የንግድ ተቀማት ላይ የበር ለበር ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስዱም የቢሮው ሃላፊ አስታውቋል።

ዘጋቢ ፦ ጦያር ይማም ከሚዛን ቅርንጫፍ