በቀጣይ ያሉ ወራቶች ለወባ መራቢያ አመቺ ጊዜያቶች በመሆናቸው ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደረግ ይገባል – ዶ/ር ደሳለኝ ዋኤ

በቀጣይም ያሉ ወራቶች ለወባ መራቢያ አመቺ ጊዜያቶች በመሆናቸው ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ በሀዋሳ ከተማ የአዳሬ ጤና ጣቢያ ጠቅላላ ሀኪም ዶ/ር ደሳለኝ ዋኤ ገልጸዋል፡፡

በስፋት ከሚሰራጩ በሽታዎች መካከል የወባ ወረርሽኝ ዋነኛው መሆኑንም ከደሬቴድ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡

በቅድሚያ ስለበሽታው ምንነት መረዳት የመጀመሪያው እንደሆነ የሚያስረዱት ዶ/ር ደሳለኝ የወባ በሽታን የሚያስተላልፉ የወባ ትንኞች እንዴት እንደሚራቡ ለይቶ ማወቅ ለመከላከል ያግዛል ነው ያሉት፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በበሽታው የመያዝ እድላቸው ሰፊ እንደሆነና ወቅቶችም ለበሽታው ስርጭት መጨመር ዋነኛ መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡

በዚህም አካባቢው ላይ ያለው ስርጭት ከፍተኛ እንደሆነ ካረጋገጡ በበሽታው ከመያዛቸው በፊት በአካባቢያቸው ባለ ጤና ጠቢያ በመሄድ ቅድመ ጥንቃቄ መውሰድም ቀዳሚ አማራጭ ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡

በበሽታው ስርጭት ላይ የሚደረገው ቁጥጥር እንዳለ ቢሆንም ስርጭቱ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ለመምጣቱም ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የሚንቀሳቀስ የህዝብ ቁጥር መጨመር እንደ ምክንያትነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

ቅድመ መከላከል ለማንኛውም በሽታ ዋነኛ መሰረት እንደሆነ በመጠቆም ሰዎች በተለምዶ የወባ በሽታ ነው በማለት ከፋርማሲ መድኃኒት በመግዛት በሽታውን በአግባቡ አለመታከም ችግሮች እንደሚስተዋሉም አመላክተዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ደሳለኝ ገለጻ የወባ በሽታ ከሚያመጣው ችግር መካከልም ታማሚው ሳይታከም በሽታው በሚቆይበት ጊዜ የቀይ ደም ሴሉ በመዳከም ለደም ማነስ የመጋለጥ እድል እንዳለውና በተለይም ህጻናት፣ በዕድሜ የገፉ ነፍሰ ጡር እናቶች የደም መጠናቸው ዝቅ በሚልበት ጊዜ በልብ ድካም የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ከመሆን ጋር ተያይዞ እስከ ሞት የሚያደርስ በሽታ ነው፡፡

በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የአዳሬ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ደግፌ በልጉዳ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ ጤና ጣቢያው ስርጭቱን ለመግታት በሚያደርገው ጥረት ድጋፍ በማድረግ የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወረርሽኙ ከባለፉት ወራት ሲነጻጸር ከፍ እያለ መምጣቱን የገለጹት ኃላፊው ለስርጭቱ እንደ ምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል የወራቶች ምቹ የአየር ሁኔታ፣ የተቆራረጠ ዝናብ፣ የሀይቅ ዳር አካባቢ ያሉ የጽዳት ችግሮች፣ በህረተሰቡ አካባቢ ያሉ ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ የወዳደቁ እቃዎች፣ እንሰት ላይ የሚቆይ ወሃ በዋናነት አንደሚጠቀሱ ገልፀዋል፡፡

ጤና ጣቢያው አገልግሎቱን ተደራሽ በሚያደርግባቸው ሁለት ቀበሌያት ላይ የቤት ለቤት ህክምና አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም በጤና ጣቢያው በሽታው የተገኘበት ሰው በሚመጣበት ወቅት የታማሚው መኖሪያ አካባቢ ባለሙያ በመላክ ምልክት በሚታይባቸው ሰዎች ምርመራ በማድረግና የመራቢያ ቦታዎችን በመለየት የስርጭቱን መጠን ለመቀነስ እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

ከህብረተሰቡ ጋር በዋናነት እየተሰራ ያለው የመከላከል ስራን ከመዘጋጃ ጋር በመጣመር የጽዳት ስራዎች ከክልል እንዲሁም ከቀበሌ አመራሮች ጋር በጋራ እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የኬሚካል ርጭት እና የአጎበር አጠቃቀም ግንዛቤ እንደሚሰጥ በመግለጽም እስካሁን ባሉት ጊዜያት ውስጥ ጤና ጣቢያው ከ3500 በላይ አጎበር ለማህበረሰቡ ስርጭት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ብዙነሽ ዘውዱ