ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሥራ አጥ ወጣቶችን ለይቶ ወደ ሥራ ማስገባት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ የዳውሮ ዞን አስተዳደር ገለጸ።

የ2017 በጀት አመት የሥራ ፈላጊ ወጣቶች ልየታና ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫ ላይ ከዞኑ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።

የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ እና የገቢዎች ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ አስፋው ደሳለኝ፥ አንድ ሀገር ኢኮኖሚ እድገት መለኪያ ዋናው አምራች የሰው ኃይል ቁጥርና ጥራት መጨመር እንዲሁም የሚሠማሩበት የሥራ መስክ ማዘጋጀትና ለምርታቸው ገበያ ማመቻቸት እንደሆነ ገልጸዋል ።

በዞኑ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን የገቢ ማስገኛ በማድረግ ሥራ አጥ ወጣቶችን ጉልበትና ክህሎት እንደ ዝንባሌቸው በማደራጀት ወደ ሥራ ማስገባት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

ይህን ለማሳካትና የሚደረገውን ጥረት ለማስቀጠል የተደራጁ ወጣቶችን ውጤታማ ለማድረግ በበጀት፣ በስልጠና፣ ማምረቻና መሽጫ ቦታ በማመቻቸት ድጋፋቸውን እንደማይቋረጥ አረጋግጠዋል።

የዳውሮ ዞን ሥራና ክህሎት፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ይርጉ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ከምንም በላይ በትኩረት እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል።

የዞኑ ሥራና ክህሎት፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ የከተማ ዘርፍ ኢንተርፕራይዞች  ደይሬክተር የሆኑት አቶ ንጉሤ ዶግሶ ለምክክር መድረክ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን ሥራ አጥ ወጣቶችን ወደ ሥራ ማስገባት የባለድርሻ አካላት ውዴታ ብቻ ሣይሆን ግደታም ስለሆነ አንገብጋቢ ነው ብለዋል።

ሥራ አጥነት ከሚያባብሱ ነገሮች ዋናው የቢዝነስ ክህሎት ልማት ያለማዳበር፣ የተደራጀ ተቋማዊ አሠራር ጉድለትና ወጣቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጤናማ ግንኙነት ማጣት እንደሆነም ጠቁመዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ወጣት ታክሰው ታደለ ፒቶታ ፈሳሽ ሣሙና አምራችና ወጣት ጌትነት አስፋው ኳሊት ማተሚያ ሥራ ማህበር ሰብሳቢ በሥራቸው ውጤታማ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በቀጣይ የሥራ አጥ ወጣቶችን በከተማም ሆነ በገጠር በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ በማደራጀትም ሆነ የተደራጁትን ውጤታማ የማድረግ ሥራ በልዩ ትኩረት ድጋፍና ክትትል ቢደረግ አካባቢውን ብሎም አገርን መለወጥ የሚያስችል የወጣቶች አቅምና ሀብት በዞኑ እንዳለ ጠቁመዋል።

የወጣቱን ግንዛቤና ክህሎት በማሣደግ፣ ለሥራ የተዘጋጁትን በመለየት፣ ወደ ሥራ ማስገባትና እየሠሩ ያሉትን በመደገፍ ረገድ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት በትጋት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም  አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፡ ኢያሱ ዶላንጎ – ከዋካ  ጣቢያችን