“የስኬታችን መሰረቱ የዛሬ ሥራችን ነው”

በአንዱዓለም ሰለሞን

ሁላችንም ልጆች ሆነን መሆን የምንፈልገው ነገር ይኖራል፤ ስናድግ እንዲህ እንሆናለን የምንለው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የዛሬው ባለታሪካችን ያጫወተኝ ነገር አለ፤ “ልጅ ሳለሁ፣ ሳድግ መምህር እሆናለሁ የሚል ምኞት ነበረኝ” በማለት፡፡ ይህ ምኞቱ ምን ያህል በውስጡ እንደሰረፀ የሚጠቁመውን አንድ ነገርም እንዲህ ሲል አወጋኝ፡-

“በአካባቢያችን የኖራ ድንጋይ አለ፡፡ እሱን እንደ ቾክ ተጠቅሜ ግድግዳ ላይ ስዕሎችን መሳልና መጻፍ ያስደስተኝ ነበር፡፡ ይህን ሳደርግም ራሴን ልክ እንደ አስተማሪ በመቁጠር ነበር፡፡”

ከመምህርነቱ ምኞት ባሻገር በልጅነቱ የሚያስደስተውን ነገር በማስታውስም እንዲህ አለኝ፡-

“የተለያዩ ስዕሎችንና ቅርጻ ቅርፆችን እሰራ ነበር፡፡ ሥራዎቼ በትምህርት ቤታችን እንደ ትምህርት መርጃ መሳሪያ በመሆን ይቀመጡ ነበር።”

ይህ በውስጡ የታመቀ የፈጠራ ችሎታ እንዳለው አመላካች ነገር መሆኑን የተገነዘበው ግን ዘግይቶ ነበር፤ ካደገ በኋላ፣ ወደ ፈጠራ ሥራ ማዘንበሉ ሲታወቀው፡፡ በዚህ ጊዜም ራሱን የልጅነት ምኞቱን እየኖረ አገኘው፡፡

እርግጥ ነው፤ ነገሩ ተኝተን እንቅልፍ ሲወስደን፣ ቀን በእውናችን ያሰብነውን ነገር ማታ በህልማችን እንደ ማየት (እንደመቃዠት) ዓይነት አልነበረም፡፡ ይህ ውጣ ውረዶችን ተቋቁሞ ተግቶ በመስራት እንጂ ተኝቶ በማለም የሚሆን ነገር አይደለምና፡፡ 

የዛሬው ባለታሪካችን ባጢሶ በየነ ይባላል። ትውልድና ዕድገቱ በሲዳማ ክልል፣ ሰሜን ዞን፣ ብላቴ ዙሪያ ወረዳ፣ ሼሎ አቦሬ ቀበሌ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በሌላ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተከታትሏል፡፡ የ9ኛ ክፍል ትምህርቱን ደግሞ በይርባ፣ ቦርቻ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተማረ በኋላ 10ኛ ክፍልን ወደ ሀዋሳ በመምጣት በአላሙራ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመማር አጠናቋል፡፡

ከዚያም በሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በኮንስትራክሽንና ቴክኖሎጂ ማናጅመንት በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ በመቀጠል በአርቤጎና ቴክኒክ ኮሌጅ በአሰልጣኝ መምህርነት ተቀጥሮ ለሁለት ዓመታት ሰራ፡፡ ይህን ጊዜም የአንደኛው የልጅነት ምኞቱ የስኬት ጅማሮ ሆነ።

ሁል ጊዜም ራሱን ለማሻሻል የሚጥረው ይህ ወጣት፣ ከስራው ጎን ለጎን በዲላ ዩኒቨርሲቲ በመማር የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ ከዚህ በኋላ በሀዋሳ ተግባረ ዕድ ኮሌጅ  በመምህርነት ተቀጠረ፡፡ በዚህ ተቋም ሳለም ሁለተኛውን የልጅነት ምኞቱን ለማሳካት ዕድል አገኘ፡፡ ሥራው ከቴክኖሎጂ ጋር የተገናኘ ነበር፤ ማስተማርና ማህበራትን መደገፍ፡፡ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ሲያስታውስም፡-

“በእርግጥም ይህ ለእኔ ጥሩ ዕድል ነበር። ውስጤ የነበረውን የልጅነት ህልሜን የበለጠ እንዳስብና የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ለመስራት ጥረት እንዳደርግ አነሳስቶኛል” በማለት በወቅቱ የተሰማውን ስሜት ይገልጻል፡፡

ባጢሶ ትውስታውን ማጋራቱን ሲቀጥልም፦

“በቴክኖሎጂ የመጀመሪያውን ሥራዬን የሰራሁት ለሽመና ሥራ የሚያገለግል ማዳወሪያ ነበር፡፡ ከምንደግፋቸው ማህበራት ውስጥ የሽመና ሥራ የሚሰሩ ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት መሳሪያ (ማዳወሪያ) ብዙም ምቹ አለመሆኑን ታዘብኩ፡፡ ከዚያም የተወሰኑ ነገሮችን በማስተካከልና በመለወጥ ለምን የተሻለ ነገር አልሰራም ስል አሰብኩ፡፡ ሙከራዬ ተሳክቶም የተሻለ ነገር ለመስራት ቻልኩ” ይላል፡፡

ከዚህ በኋላ በእርሻ፣ በግብርና፣ በግንባታ እንዲሁም በእንጨትና ብረታ ብረት ዘርፍ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለመስራት መቻሉን ይገልፃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ለአብነት ለመጥቀስ ያህል የአሸዋ ማበጠሪያ እና የጣውላ መሰንጠቂያ ማሽኖች ያገኛሉ፡፡

የአሸዋ ማበጠሪያ ማሽኑ በግንባታ ዘርፍ ያለን አንድ ችግር ለማቃለል የሚረዳ መሆኑን ባለታሪካችን ይገልጻል፤ “ማሽኑ የተቀላቀለውን አሸዋና ጠጠር ለመለየት ያስችላል” በማለት፡፡

የጣውላ መሰንጠቂያውን አስመልክቶ ሲናገርም፣ አብዛኞቹ የማህበሩ አባላት የሚጠቀሙት በማኑዋል የሚሰራ ማሽን መሆኑን እንደታዘበና ይህም የተሻለ ማሽን ለመስራት እንዳነሳሳው ይናገራል፡፡

ሌላው እዚህ ላይ የሚጠቀሰው፣ ሀገር በቀል ዕውቀትን አስመልክቶ፣ በተለይም የሸክላ ሥራ ላይ የተሰማሩ ማህበራት ያለባቸውን ችግር ለመቅረፍ በሚል የሰራው ስራ ነው፡፡

“ይህ የስራ ዘርፍ ጉልበት ዝም ብሎ የሚባክንበት ነው” የሚለው ባጢሶ፣ ከሌሎች የስራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ለባለሙያዎቹ ለስራቸው ምቹ የሆነ ማሽን መስራት መቻላቸውን ይናገራል፡፡

ማሽኑን በተመለከተ ሲናገርም፣ አፈሩን ለመፍጨት፣ ለማቀላቀል፣ ለማዋሀድና ለማቡካት ብሎም በተለያየ ዓይነት መልኩ ቅርጽ ለማውጣት እንደሚያስችል ገልጿል፤ ይህ ደግሞ የባለሙያዎችን ድካም የሚቀንስና ጊዜያቸውንም የሚቆጥብ ከመሆኑም ባሻገር የተሻለ ሥራ ለመስራት እንደሚያስችላቸው በመጠቆም፡፡

ከእነዚህ ሥራዎቹ ባሻገር በግሉ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ አብዛኛውን ጊዜውንም የተሻለ ስራ ለማስራት ጥረት በማድረግ ያሳልፋል፡፡ ከዚህ ተሞክሮው በመነሳት ለመሥራት ከታሰበ ብዙ ነገር ለመስራት እንደሚቻልና በብዙ መልኩ ለውጥ ለማምጣት እንደሚቻል አበክሮ ይናገራል፡፡

ከምንም በላይ ግን የግብርና ሙያን ከማዘመን አንጻር የሰራው አንድ የፈጠራ ስራው በፌደራል ደረጃ ለመወዳደር ያስቻለውን አጋጣሚ እንደፈጠረለትና ይህም በእጅጉ እንዳስደሰተው ይገልጻል፡-

“የፈጠራ ስራ ያላቸውን ወጣቶች የሚጋብዘውን የውድድር ማስታወቂያ ከማስታወቂያ ቦርድ ላይ ነበር ያየሁት፡፡ ለዚህ ውድድር የመረጥኩት ሥራዬ የአርሶ አደሩን 7 መሰረታዊ የምላቸውን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል የእርሻ መሳሪያ ነበር፡፡ ማረስ፣ መከትከት፣ መዝራት፣ ውሀ ማጠጣት፣ ማጨድ፣ ለመጓጓዣነት ማገልገል ማሽኑ ከሚሰጣቸው ጥቅሞች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ 

በወርሀ ሀምሌ፣ 2015 ዓ/ም የኢትዮጵያ  ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ያመቻቸውን ዕድል በመጠቀም ይህንን ስራውን በመያዝ ለውድድር ቀረበ፡፡  ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተውጣጡና የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን የሰሩ 520 ባለተሰጥኦዎች በተሳተፉበት በዚህ መድረክ ባለታሪካችን ስራው ተቀባይነትን አግኝቶለታል፡፡ በቆይታው ስለነበረው ሁኔታ ሲገልጽም፡-

“በቆይታዬ ብዙ ልምድና እውቀት አግኝቻለሁ፡፡ ብቃታችንን ሊያሳድጉ የሚችሉ የተለያዩ ቴክኒካል ስልጠናዎች ተሰጥተውናል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ እንደ እኔ ዓይነት የፈጠራ ሥራ ከሰሩ አምስት ሰዎች ጋር መገናኘቴና በጋራ ሆነን አንድ ውጤታማ ሥራ እንድንሰራ መደረጉ በጣም አስደስቶኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ሥራውን ጀምረነው ጥሩ ሂደት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ቢዝነስ ፕላን ሰርተን ለልማት ባንክ ካስገባን በኋላ ብድር ተፈቅዶልናል፡፡ ዓላማችን በጋራ ሆነን የሀገራችንን አርሶ አደሮች ችግር የሚያቃልል አንድ ጥሩ የፈጠራ ስራ መስራት ነው። ይህ እንደሚሳካም ተስፋ አለኝ” ብሏል፡፡

ወጣቱ በስሜት ተውጦ ይህን ሲያጫውተኝ፣ ስራው ምን ያህል ውጤታማና አዋጭ እንደሆነ በተለይም ደግሞ ከተደራሽነት አኳያ ስላለው ነገር ጥያቄ ማንሳቴ አልቀረም፡፡ እሱም እንደዚህ በማለት ምላሹን ሰጠኝ፡-

“አዋጭነቱም ሆነ ውጤታማነቱ ተረጋግጧል። ከዋጋ አንጻር ስንመለከተውም አነስተኛ ብር የሚፈጅና ትርፋማ ነው፡፡ ከውጪ ከሚገባውና አንድ ዓይነት አገልግሎት ከሚሰጠው ጋር ሲተያይ የተሻለና ዋጋውም በጣም ቅናሽ ነው፡፡ በአጠቃላይ በብዙ መልኩ ስንመለከተው ማሽኑ ተመራጭና ተፈላጊ የሚሆንባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። ማሽኑን የሚገዛው መንግስት ነው፡፡ ያም ሆኖ ማሽኑን በብዛት ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ገንዘብ እንደሚያስፈልገን ግልጽ ነው፡፡ ከህብረተሰቡ 85 በመቶ የሚሆነው አርሶ አደር እንደ መሆኑ ባለሀብቶች ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ከባለታሪካችን ጋር በነበረኝ ቆይታ ማብቂያ ላይ አንድ ጥያቄ አነሳሁለት፤ ስለ ወደ ፊት ዕቅዱና ምን ማድረግ እንደሚያስብ እንዲነግረኝ፡፡ እርሱም እንዲህ ሲል ስለቀጣይ ዓላማው አጫወተኝ፡-

“አሁን ነገሮች በጥሩ መልኩ እየሄዱ ነው። የጀመርነውን ሥራ በጋራ እየሰራን ነው። የጀመርነውን ጨርሰን፣ ውጤቱን እንደምናይ ተስፋ አለኝ፡፡ ይህ ነገን በተስፋ ለመጠበቅ የሚያደርግ መልካም ነገር ነው፤ የበለጠ ነገር ለመስራት እንደምችል የሚያስገነዝበኝ ጭምር ነው፡፡ በቀጣይ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ፣ የራሴን ትልቅ ካምፓኒ የማቋቋም ህልም አለኝ፤ እንደሚሳካም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይኸው ጀመርነው አይደል? “የስኬታችን መሰረቱ የዛሬው ሥራችን ነው፡፡”

እርግጥ ነው፤ የዛሬ ጅምራችን የነገ ስኬታችን መሠረት ነው፡፡ የሚያጋጥሙንን ውጣ ውረዶች ታግሰን ከጣርንም ካሰብንበትት ለመድረስ ይቻለናል፡፡ ለዚህ ደግሞ “ባጋጠሙኝ ችግሮች ተስፋ ብቆርጥ ኖሮ እነዚህን የልጅነት ምኞቴ የሆኑትን ነገሮች መስራት አልችልም ነበር” የሚለው የዛሬው ባለታሪካችን የህይወት ተሞክሮ አንድ ማሳያ ነው፡፡