የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ከማጠናከር ባለፈ ጤናማ ንቁና የተሻለ ስብዕና ያለው ትውልድ ለመፍጠር የቴኳንዶ ስፖርት ትልቅ ሚና እንዳለው ተመላከተ

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ከማጠናከር ባለፈ ጤናማ ንቁና የተሻለ ስብዕና ያለው ትውልድ ለመፍጠር የቴኳንዶ ስፖርት ትልቅ ሚና እንዳለው ተመላከተ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 06/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ከማጠናከር ባለፈ ጤናማ ንቁና የተሻለ ስብዕና ያለው ትውልድ ለመፍጠር የቴኳንዶ ስፖርት ትልቅ ሚና እንዳለው ተመላክቷል፡፡

ይህ የተገለፀው የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንድ ፌደሬሽን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለተወጣጡ ለዘርፉ ስፖርተኞች የ2ኛ እና የ3ኛ ደረጃ የዳኝነት ስልጠና በወልቂጤ ከተማ በሰጠበት ወቅት ነው፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ቶፊቅ ነስሩ እና አልፊያ ነስሩ እንደተናገሩት፤ ስልጠናው ያላቸውን አቅም በማሳደግ በቀጣይ በዘርፉ የተሻለ ውጤታማ እንዲሆኑ እያገዛቸው ይገኛል፡፡

የቴኳንዶ ስፖርት ራሳቸውን ለመከላከልና ለመጠበቅ የሚያስችላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀምና ከአልባሌ ነገሮች ለመራቅ እንደሚያስችላቸው ገልፀዋል፡፡

ሰልጣኞች የቴኳንዶ ስፖርት የዳኝነት ህጎችን በአግባቡ በመረዳት በዳኝነት ወቅት የሚፈጠሩ ስህተቶችን ለመቅረፍ የሚያስችላቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝና ኢንተርናሽናል ዳኛ ማስተር ለሜሳ ቡሩክ በዚህ ወቅት አስታውቀዋል፡፡

የኡንጀሞ ወርልድ ቴኳንዶ ማሰልጠኛ ማዕከል ሃላፊና ኢንተርናሽናል ዳኛ ሳቦም ሀዲሙ አክመል የክልሉና የፌዴራል ወርልድ ቴኳንድ ፌደሬሽን እንዲሁም የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር የስራ ሃላፊዎች እያደረጉላቸው ላለው የቅርብ ድጋፍና ክትትል ምስጋናውን አቅርቧል ፡፡

የኡንጀሞ ወርልድ ቴኳንዶ ማሰልጠኛ ማዕከል በክልልና በፌደራል ደረጃ ብቃት ያላቸው ተወዳዳሪዎችን በማፍራት ውጤታማ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የቀቤና ልዩ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጁሃር ጀማል ተናግረዋል፡፡

ጥሩ ስነ-ምግባር የተላበሰና ታዛዥ ትውልድ ለመፍጠር የቴኳንዶ ስፖርት ትልቅ ሚና ይጫወታል ያሉት ሃላፊው በልዩ ወረዳው ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በክልሉ የሚታየውን የአሰልጣኞች እጥረት ለመቅረፍ ስልጠናው አገዥ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቴኳንድ ስፖርት ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ሱልጣን ጁሃር ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንድ ፌደሬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፍቅሩ ተቋም ሀገሪቱን በአለም አቀፍ ደረጃ በወርልድ ቴኳንድ ስፖርት ዘርፍ የተሻለ ተወዳዳሪና ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ ተወዳዳሪዎችና አሰልጣኞች አቅም ማሳደግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ስፖርቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ከማጠናከር ባለፈ ጤናማ ንቁና የተሻለ ስብዕና ያለው ትውልድ ለመፍጠር ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

በቀቤና ልዩ ወረዳ የሚገኘው ኡንጀሞ ወርልድ ቴኳንዷ በፌደራልም ሆነ በክልሉ ውጤታማ እንቅስቃሴ በማድረግ ለሌሎች በአረዓያነት የሚጠቀስ መሆኑንም በመጠቆም፡፡

በስልጠናው ከቀቤና ልዩ ወረዳ ጨምሮ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተወጣጡ የዘርፉ ስፖርተኞች ተሳትፈዋል፡፡

ስልጠናው ለ3 ተከታታይ ቀናት የተሰጠ ሲሆን የአቅም ምዘና ፈተናና የእውቅና ሰርተፍኬት በመስጠት ተጠናቋል፡፡

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን