ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ኀጢአትና በደል ይቅር ባይነቱን፣ ቸርነቱን፣ ፍቅሩን፣ ትህትናውንና መልካምነቱን ነብሱን እስከ መስጠት በቀራንዮ መስቀል አሳይቷል – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ኀጢአትና በደል ይቅር ባይነቱን፣ ቸርነቱን፣ ፍቅሩን፣ ትህትናውንና መልካምነቱን ነብሱን እስከ መስጠት በቀራንዮ መስቀል አሳይቷል – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 26/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለትንሳዔ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የርዕሰ መስተዳድሩ እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ኀጢአትና በደል ይቅር ባይነቱን፣ ቸርነቱን፣ ፍቅሩን፣ ትህትናውንና መልካምነቱን ነብሱን እስከ መስጠት በቀራንዮ መስቀል አሳይቷል።

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁላችን ኃጢያት ስርየት ሲል በመስቀል ላይ የተሰቀለበት፣ በሰው ልጆች እና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የሞትና የጥል ግድግዳ አፍርሶ ዳግም ዘላለማዊ ህይወት የሰጠበት እለት በመሆኑ ለዚህ ታላቅ መንፈሳዊ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ የኃጢያት ቤዛ በመሆን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መሞቱና በሦስተኛው ቀን ከሞት በመነሳት የትንሳዔን ህይወት የሰጠን እሱ ለፈጠረው ለሰው ልጆች ሁሉ ያለውን ታላቅ ፍቅሩን የገለፀበት ዋነኛው መንገድ ነው።

የኢየሱስ ክርስቶስ ትልቁ ስጦታው የዘላለም ህይወት ነው፤ ይህንን የዘላለም ህይወትን ያገኘነው በመስቀል ላይ ሞት ነው፤ የመስቀል ላይ ሞቱን የፈፀመው ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ሲል ነው፤ እኛም ፍቅር ትልቅ ትርጉም እንዳለው መረዳት ያስፈልገናል፤ እንድንዋደድ እንድንፋቀር ፈጣሪ በቃሉ መክሮናል አዞናልም፡፡ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ ብለው ፈጣሪ በቃሉ ነግሮናል። ከእነዚህ የሚበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለም። ስለዚህም እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ያስፈልገናል።

በፍፁም ልባችን እየተዋደድን፥ እየተሳሰብን፥ እየተረዳዳን፥ እየተጋገዝን ከሆነ ፍቅር መኋላችን አድሮዋል ማለት ነው።

ስለሆነም ፍቅር ለሰው ልጆች ሁሉ የሰላም ምንጭና መሰረት በመሆኑ በዓሉን ስናከብር ከጥላቻ ርቀን አንዳችን ለአንዳችን ያለንን በጎነትና ፍቅርን የምንገልፅበትና የምንተሳሰብበት ዕለት እንዲሆን እመኛለሁ።

የሁላችንም የሆነችሁ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንድትበለጽግ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ መስቀል ሆኖ በተግባር ባሳየን ትህትናና ፍቅር መሰረት ከግላዊ ጥቅምና ፍላጎት ተላቀን፤ እርስ በርሳችን በመተጋገዝና በመተሳሰብ ህዝባዊ ጥቅምን አስቀድመን ለችግሮችና ለፈተናዎች ሳንበገር የሀገራችን የልማትና የብልፅግና ትንሳዔዋን አናፋጥን እላለሁ።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በመስቀሉ ፍቅርን፣ ትህትናን፣ መልካምነትን፣ ሩህሩህነትን እና ለሌሎች ስንል መስዋዕትነት መክፈልን አስተምሮናል።

እሱ ባስተማረን ፍቅርና ርህራሄ በአካባቢያችንና በዙሪያችን አቅመ ደካማዎችና ረዳትና ጠዋሪ የሌላቸው አረጋውያንን ያለንን በማካፈል፣ በመርዳትና በመደገፍ በዓሉን በደስታ እናክብር እላለሁ።

በድጋሚ እንኳን ለትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!!

አቶ ደስታ ሌዳሞ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር

ሚያዝያ 26/2016 ዓ.ም