ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 26/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለስቅለትና ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ መግለጫ

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ!

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ የትንሳኤን በዓልን በማስመልከት ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንደገለጹት የትንሳኤ በዓል እየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለውን ፍጹም ፍቅር እና አክብሮት በህማማቱ፣ በስቅለቱ፣ በሞቱ እና በትንሳኤው የገለጸበት ነው።

ይህ በዓል በህዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ በፆም፣ በስግደት እና በምስጋና የሚከበር፣ በንስሃ በንፁህ ህሊና እና በአርምሞ ወደ ፈጣሪያቸው የሚቀርቡበት ታላቅ በዓል መሆኑ እጅግ ልዩ እና ተናፋቂ ያደርገዋል።

ምእመናን የምስጋና፣ የፆም፣ የስግደት እና የንስሀ ቀናትን በመንፈሳዊ በረከት አሳልፈው እነሆ ትንሳኤ ሊሆን በስቅለቱ ዕለት ላይ እንገኛለን።

የዘንድሮውን የትንሣኤ በዓል የምናከብረው የሠላም የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት እንዲሁም በብዝሀነት ውስጥ የአንድነት ማዕከል የሆነው ክልላችንን በህዝቦች ይሁንታና መፈቃቀድ መስርተን ፈጣን የልማት የእድገትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን እያከናወንን በሚገኝበት ዓመት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

የክልሉን ሰፊ የመልማት አቅም በመጠቀም የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መደበኛ የልማት ስራዎች እና መንግስት የቀረፃቸው የእድገት ኢንሼቲቮች ክልላዊ ይዘት ያላቸው አዳድስ አስተሳሰቦችን በማከል ሁሉንም አካታች ባደረገ መልኩ ግብ ጥለን ህዝቡን በማሳተፍ እየሰራን ተምሳሌት የሆኑ ውጤቶችንም እያስመዘገብን እንገኛል።

አምላክ የቸረንና በክልላችን የሚገኙ የተፈጥሮ ፀጋዎችን ለህዝብ የላቀ ተጠቃሚነት ማዋል የምንችለው በስግብግብነት እርስ በርስ በመናቆር ሳይሆን እይታችንን በማስፋት፣ ክንዶቻችንን በማበረታት፣ ዕውቀታችንን ክህሎታችንንና ሀብታችንን በማስተባበርና በመደመር ነው

ህዝበ ክርስትያኑ ከትንሳኤ በአል ጋር ባላቸው የላቀ ቁርኝት በፆም በስግደት በሚከወኑ መንፈሳዊ ክዋነዎች ህብረተሰባችን አንድነትን የሚገነባበት ሰብአዊነትን፣ ልግስናን፣ ቸርነትን፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች መኖርን፣ ይቅርታን፣ ምህረት ማድረግን፣ ህብረትንና አንድነት ይማራል።

በእየሱስ ክርስቶስ አስተምሮ መሰረት ጥላቻን ነቅለን ፍቅርን እየተከልን፤ አንዳችን ለሌላችን አቅም እና ጉልበት እየሆንን፣ እንደ ድርና ማግ በመተሳሰብ ተሸምነን የጀመርነውን የሰላም የመቻቻልና የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን መላው የክልላችን ህዝብ ተግቶ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

“የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ መነሳት ለሰው ልጆች ያለው አስተምህሮ በጣም ብዙ ነው፣ በእውነትና በቅንነት እንድንኖር፣ ክፋትና ምቀኝነትን፣ ግፍ በደልና ጥላቻን፣ ተንኮልን ሴራን በማስወገድ በጽድቅ እንድንኖር ነው” ብለዋል።

አንድነታችንን እና ህብረታችንን ካጠናከርን የገዘፈ የመሰለንን ጊዜያዊ ችግር በቀላሉ መሻገር እንችላለን ለዚህ ደግሞ የመላው ህዝባችንን የላቀ ተሳትፎና ድጋፍ ይጠይቃል በማለት ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው አክለው እንዳሉት በተለያዩ ምክንያቶች እየተከሰቱ ያሉ የሸቀጦች ዋጋ ንረት እና ምርትና ምርታማነትን በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት አለማደግ ተዳምሮ የኑሮ ውድነት ህዝባችንን እየተፈታተነ ነው ብለዋል።

መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት መላው ህዝባችንን በማሳተፍ በከተማ እና በገጠር የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ እንሸትቮችን በመቅረጽ እያካሔደ ያለው ጥረት ሊጠናከር እንደሚገባ በሁሉም ዘርፍ ምርታማነትን በፍጥነት ስናሳድግ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥርልን ይሆናል ሲሉም በመልዕክታቸው አውስተዋል።

በሌላ በኩል ለኑሮ ውድነቱ መንስኤ የሆኑ ሰው ሰራሽ ችግሮችን መፈተሽና ማረም ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚስተዋለውን ህገ ወጥነት በመከላከል ረገድ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ሊሆን ይገባል ሲሉም አብራርተዋል።

የትንሳኤ በዓልን ከመብላትና ከመጠጣት በላይ ለአፍታም መዘንጋት የሌለበት እገዛ ለሚፈልጉ አቅመ ደካሞችን፣ በማረሚያ ቤት የሚገኙትን፣ የታመሙትን፣ በመጠየቅና በመደገፍ ይህን ወቅት መሻገር እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት የሰላም፣ የፍቅር እና የአብሮነት በዓል እንዲሆን ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በድጋሚ መልካም በዓል ይሁንላችሁ !

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

አቶ ጥላሁን ከበደ

ምንጭ ፡ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ