በኢትዮጵያ ምርጡ ጋዜጠኛ ለመሰኘት እየተወዳደረ ያለው የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ባልደረባ -ጋዜጠኛ ወንድዬ ካሳ
ትውልዱ ወሎ ላስታ ነው ። ዕድገቱና ትምህርቱ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ነው። በንግግር እጅግ ቁጥብ ሲሆን ብዕሩ ግን እጅግ ስል ናት።
በስራም ቦታም ሆነ በስብሰባ አዳራሾች ድምፁ ብዙም አይሰማም። የውስጥ ሀሳቡንና ጩኸቱን ወረቀት ላይ ማስፈር ይችልበታል። ማህበራዊ ሂሶቹ ደግሞ ነጩን” ነጭ” ጥቁሩን ”ጥቁር” የሚሉ በመሆናቸው በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፈውለታል።
ወንድዬ ካሳ ደራሲም ጋዜጠኛም ነው።
የዛሬ የበዓል ልዩ እንግዳችን ወንድዬ ካሳ በደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጀት ውስጥ ከሚገኙ ስመጥር ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው።
ጋዜጠኛ ወንድዬ ካሳ የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የውስጥ መሻቴን ወደ ተግባር እንድለውጥ ያስቻለኝ በመሆኑ ውለታው አለብኝ ይላል ።
ጋዜጠኛ ወንድዬ በድርጅቱ የመገናኛ አውታሮች በጋዜጣ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ አማራጮች ሰርቷል። ነገር ግን ስሙን መትከል የቻለው በሬዲዮ ዘርፍ ”የጥበባብ ምሽት” በተሰኘ ኘሮግራም ላይ በሚያቀርባቸው ልዩ ወጎች ነው።
”የጥበባት ምሽት” 2004 ዓ/ም አከባቢ በጋዜጠኛ ወንድዬ ካሳና በባልደረቦቹ የተጀመረ ሲሆን አሁንም በተወዳጅነት ቀጥሎ ሕዝብ እያዝናና በማስተማር ላይ ይገኛል።
ጠንካራ ማህበራዊ ሂስ መሠንዘር የጥበባት ምሽት የወግ ኘሮግራም ልዩ ምልክት ነው። የወንድዬ ወጎች ደግሞ የፕሮግራሙ የጀርባ አጥንት ናቸው ይላሉ ባልደረቦቹ እና የፕሮግራሙ ወዳጆች።
ወጎቼ ማንንም የማስቀየም አልያም የማስደሰት አላማ የላቸውም የሚለው ጋዜጠኛ ወንድዬ ካሳ በህብረተሰቡ ውስጥ የማያቸው ጉድለቶች እንዲታረሙ ከመፈለግ የመነጨ ሃሳብ ብቻ ነው ያለኝ በማለት ይገልፃል።
ጋዜጠኛ ወንድዬ አሁን ላይ በኢትዮጵያ የአመቱ ምርጥ ጋዜጠኞን ለመምረጥ እየተካሄደ ባለው “ክብር አዋርድ” ላይ በዕጩነት ቀርቦ እየተወዳደረ ይገኛል። ”በዚህ ክብር ሽልማት ላይ ስራዬ ታውቆ ምርጥ አምስት መግባቴ ለእኔ ክብር ነው ” በማለት ስሜቱን ያጋራን እንግዳችን በቀጣይም ያለሁበትን የሬዲዮ ጣቢያም ሆነ አድማጩን ይበልጥ እንዳገለግለው ትልቅ የቤት ስራ ሰጥቶኛል እኔም ይህንኑ ማሕበረሰባዊ ሃላፊነት ተቀብያለሁ በማለት አጫውቶናል ።
በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ በርካታ የሚዲያ አውታሮች ( ብሮድካስት ) እየተከፈቱ በመሆቸው የሀሳብ ልዕልናን ለማረጋገጥ ትልቅ አውንታዊ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል።
በነባርና በአዳዲስ ሚዲያዎች የቀድሞ የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋዜጠኞች መሪ ተዋናይ መሆን መቻላቸው ደግሞ ድርጅቱ የምርጥ ጋዜጠኞች መፍለቂያ ስለመሆኑም አመላካች ነው “‘ ይላል ወንድዬ ካሳ።
ጋዜጠኛ ወንድዬ ካሳ ከመደበኛ ስራው ጎን ለጎን ሶስት ዳጎስ ያሉ መፅሃፍትን ለተደራሲያን አበርክቷል ። ሁኔታዎች ከተመቻቹ ደግሞ ለህትመት የሚበቁ የፅሁፍ ስራዎች ተሰንደው መቀመጣቸውንም ጠቁሞናል ።
የአንድ ጋዜጠኛ ስንቅና ትጥቁ ማንበብና ማንበብ ብቻ ነው የሚለው እንግዳችን ቁሳዊ ሀብት ባይኖረኞም ከንባብ ያገኘሁት ዕውቀትና ልምድ ከምንም ጋር ሊወዳደር አይችልም ባይ ነው።
ጋዜጠኛ እና ደራሲ ወንድዬ ካሳ ለመላው የክርስትና እምንት ተከታዮች መልካም የትንሳኤ በዓል እንዲሆን መልካም ምኞቱን አስተላልፏል ፡፡
በሃገር አቀፉ በክብር ሽለማት ላይ እየተወዳደረ ያለው ወንድዬ ካሳ ከታች የተቀምጠውን ማስፈንጠሪያ ( link) በመጠቀም ድምጽ እንዲትሰጡትም መልዕክት አስተላልፏል ፡፡ https://kibershilemat.com/login
አዘጋጅ ፡ ጀማል የሱፍ
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ