የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 18/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀገር ደረጃ የተስተዋለውን የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በዋናነት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራንና ሱፐር ቫይዘሮች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና በአርባምንጭ ከተማ ሰጥቷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የመማር ማስተማር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ፥ ለአንደኛ ደረጃ መምህራንና ለሱፐር ቫይዘሮች የተሰጠው የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ክህሎታቸውን ከመለካቱ ባለፈ በክልሉ የተስተዋለውን የትምህርት ስብራትን ለመጠገንና የተማሪውን ውጤት ለማሻሻል በክልሉ ከሚገኙት 70 ሺህ መምህራን መካከል ለ5ሺህ 500 ለሚሆኑ መምህራን ፈተና መሰጠቱን ተናግረዋል ።

የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ምዘና በየሶስት ዓመት የሚሰጥ መሆኑን የገለፁት አቶ ኢሳያስ የትምህርት ግብዓት እጥረት በዘለቄታ ለመፍታት እየተሠራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ አብርሃም አምሳሉ እንዳሉት የትምህርት ስብራትን ለመጠገንና የመምህራንን ክህሎት ለመለካት በዞኑ በሁሉም መዋቅሮች ለተወጣጡ ለ1ሺህ 600 መምህራን ፈተና መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

አንዳንድ የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ፈተና የተፈተኑ መምህራን እንዳሉት፥ የተሰጣቸው ፈተና ራሳቸውንና ያላቸውን ክህሎት የሚመዝኑበት መሆኑን ገልጸው በቀጣይ የመማር ማስተማር ስራቸው ላይ አቅም እንደሚፈጥርላቸው አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ: አንጃ ገልስሞ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን