ኢስላማዊ ቅዱስ የፀሎት ስፍራ
በመላው ዓለም በሚገኙ ሙስሊሞች ዘንድ እጅግ የገዘፈ ስምና ዝና ካላቸው ቅዱስ የጸሎት ስፍራዎች መካከል አንዱ አል-አቅሳ መስጊድ ነው።
አል-አቅሳ መስጊድ ፍልስጤም ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው የአል-ሀራም አሽ-ሸሪፍ ግቢ ውስጥ ይገኛል። ለሙስሊሞች ከመካ እና ከመዲና በመቀጠል በዓለም ላይ ከሚገኙ ሦስተኛው ቅዱስ ኢስላማዊ የፀሎት ስፍራ ነው፡፡
እየሩሳሌም በሙስሊሞች ዘንድ ከመካ እና ከመዲና ቀጥላ ሶስተኛዋ ቅድስት ስፍራ ናት፡፡ አል-መስጂድ አል-አቅሳ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ሙስሊሞች በታላቁ የረመዳን ወር ሐጅ የሚያደርሱበት እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የሐይማኖቱ ተከታዮች በታላቁ ረመዳን ፆም ወቅት ወደ መካ እና መዲና እንደሚጓዙት ሁሉ፥ ጓዝ ጭነው ስንቅ ቋጥረው ለጉብኝትም ሆነ ለሶላት ከሚሄዱባቸው ሦስት የፀሎት ስፍራዎች መካከል አንዱ እየሩሳሌም የሚገኘው አል-አቅሳ መስጊድ ነው፡፡
አል-አቅሳ የሚለው ስም “በጣም ሩቅ” ማለት ሲሆን ነቢዩ ሙሐመድ በምሽት የተጓዙበት ቦታ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ስፍራው ነቢዩ ሙሐመድ ወደ ሰማይ ያረገበት ቦታ ነው ተብሎ የሚታመነው በዚሁ የአል-ሐራም አሽ-ሻሪፍ ግቢ ውስጥ እንደሆነ ይነገራል፡፡
የመጀመሪያው መስጊድ አል-አቅሳ የቦታና የመስጊድ ሥም ብቻ ሳይሆን ከእስልምና ሃይማኖት ጋር የሚያገናኙት በርካታ ቁምነገሮች እንዳሉና አላህ (ሱ.ወ.) መስጂድ አል-አቅሳንና ዙሪያውን በሱ የተባረከና የተቀደሰ አካበቢ መሆኑን በቁርአን ላይ መገለፁን ኢስላማዊ አስተምህሮ ያስረዳል፡፡
ሌላው አል-አቅሳን ከሙስሊሞች የሚያስተሳስረው የኢስራ እና ሚዕራጅ ምድር መሆኑ ነው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ወደ ሰማዩ ዓለም ጉዞ ባደረጉ ጊዜ ከመካው መስጂድ ወደ እየሩሳሌም መስጂድ አል-አቅሳ ተጉዘዋል፡፡ ከዚያም በመነሳት ነበር ወደ ሰማዩ ዓለም የተጓዙት፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከመካ ወደ በይት አልመቅዲስ መጓዛቸው የቦታውን ታላቅነትና ቅድስና እንደሚያመላክት የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
በሌላ መልኩ አል-አቅሳ የመጀመሪያው የሙስሊሞች ቂብላ (የሰላት አቅጣጫ) መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለአለም ህዝብ በነብይነት ሲላኩ የሙስሊሞች ቂብላ(የሶላት መቀጣጫ) ወደ ከዕባ(መካ) እንዲሆን ከመደረጉ በፊት ለአሥራ ስድስት ወይም ለአሥራ ሰባት ወራት ወደእየሩሳሌም ወደ መስጊድ አል-አቅሳ ዞረው ሰግደዋል፡፡
በርካታ የነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች እና ትላልቅ ደጋግ ሰዎች የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እየሩሳሌም ስለሚገኘው ስለ አል-አቅሳ ደረጃና ቅድስና ያስተማሩትን በመከተል ወደዚያ ሄደዋል፡፡ ጎብኝተውታል፡፡ ሰግደውበታል፡፡
አል-አቅሳን ከጎበኙ ታላላቅ ሶሓቦች መካከል ዑመር ኢብኑ አልኸጣብ፣ አቡ ዑበይዳ፣ የምእመናን እናት ሶፍያ፣ ሙዓዝ ኢብኑ ጀበል፣ ዐብደላህ ኢብኑ ዑመር፣ ኻሊድ ኢብኑ አልወሊድ፣ አቡ ዘር፣ አቡ ደርዳእ፣ ሰልማን አልፋሪሲይ፣ ዐምር ኢብኑ አልዓስ፣ ሰዒድ ኢብኑ ዘይድ፣ አቢ ሁረይራ፣ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐምር እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
በርካታ ትላልቅ የሙስሊሙ ዓለም ሊቃውንትም ለትምህርትና ለኑሮ ወደዚያው ተጉዘዋል፡፡ ታዋቂው ሙፈሲር ሙቃቲል ቢን ሱለይማን፣ ኢማም አልአውዛዒ፣ ኢማም ሱፍያን አስሠውሪይ፣ ኢማም ለይሥ ኢብኑ ሰዕድ፣ ሻፊዒይና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
ይህና የመሳሰለው ጉዳይ አለም ላይ ያለው ሙስሊም ማህበረሰብን ከእየሩሳሌም ጋር እንደሚያስተሳስረው የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት መረጃዎችና የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆች ያመላክታሉ፡፡
አዘጋጅ፡ ብዙነሽ ዘውዱ
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ