በበጋ መስኖ ልማት በተከናወነው ስራ የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል – በሀላባ ዞን የዌራ ዲጆ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት

በበጋ መስኖ ልማት በተከናወነው ስራ የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል – በሀላባ ዞን የዌራ ዲጆ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት

ሀዋሳ፡ መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በበጋ መስኖ ልማት በተከናወነው ስራ የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ በሀላባ ዞን የዌራ ዲጆ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ።

በመስኖ ልማቱ ተሳተፊ የሆኑ አርሶ-አደሮች እንደሚሉት ከዚህ ቀደም በጎርፍ ምክንያት ይደርስባቸው የነበረው ችግር ከተቀረፈላቸው ወዲህ በልማቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

አርሶአደር ገረሙ መሀመድና ዋበላ ሸ/አህመዲን በወረዳው በስምቢጣ ቀበሌ በመስኖ ልማቱ ተሳታፊ ከሆኑ አርሶአደሮች መካከል ሲሆኑ በቀደሙት ጊዜያት ማሳቸው በጎርፍ ምክንያት ምንም ማልማት እንደማይችሉና ተሰደው በሌሎች አከባቢዎች በጥገኝነት ይኖሩ እንደነበር ተናግረዋል።

ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን ችግሩ ተቀርፎላቸው ወደቀያቸው ከተመለሱ በኋላ የተፈጠረላቸውን ግንዛቤ ወደተግባር ቀይረው ባገኙት የውሃ አማራጭ በበጋ ወራት መስኖን እያለሙ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልፀዋል።

ከራሳቸው አልፈው ለብዙሃን እያተረፉ እንደሚገኙ የሚነግሩት አርሶአደሮቹ ሌሎችም አርሶአደሮችና አካባቢዎች ከስራቸው ተሞክሮን እየወሰዱ በመስኖ ልማቱ እራሳቸውንና ሀገራቸውን መጥቀም እንደሚገባቸውም ይመክራሉ።

የስምቢጣ ቀበሌ የግብርና ባለሙያ  እንደሚሉት ለአርሶ-አደሮቹ በቅርበት ሆነው ሙያዊ ድጋፋቸውን ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመሆን እየደገፉ መሆናቸውን ተናግሯል።

የወረዳው ምክትል አስተዳደርና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎበና ሰማን እንደገለፁት የአርሶአደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የበጋ መስኖ ስራን ጨምሮ በሌሎችም የእርሻ ወቅቶች የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይ በጎርፍ ምክንያት ለስደትና ለተለያዩ አደጋዎች ይጋለጥ የነበረውን አከባቢ በየደረጃው ከሚገኙ የመንግስት መዋቅሮች ጋር በመሆን በተሰራው ስራ ችግሩ እንዲቀረፍ ተደርጎ ከቅርብ አመታት ወዲህ በመስኖ ልማት የተሻለ ስራ እየተሰራበት እንደሆነም ገልጸዋል።

እንደ ወረዳው የውሃ አማራጭ ባላቸው ስምንት ቀበሌያት ላይ ከ6 መቶ በላይ አርሶአደሮችን በማሳተፍ ከ5 መቶ የሚበልጥ ማሳ በአትክልት፣ በፍራፍሬና የበጋ ስንዴን ጨምሮ ማልማት መቻሉንም አቶ ጎበና አመላክተዋል።

ምርቱ ወደ ገበያ እንዲደርስ የገበያ ትስስር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን መፈጠሩን የተናገሩት ኃላፊው ለመስኖ ስራው ውጤታማነት አጋዥ የሆኑ የግንዛቤ፣ የግብአትና የውሃ መሳቢያ ፓምፖችን ጨምሮ መሰረተ ልማት የማሟላትና ሌሎችም አስፈላጊ ድጋፎች እየተደረገላቸው መቆየቱን ጠቁመው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ምርቱ የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት ከማረጋገጡም በላይ ገበያን በማረጋጋቱ በሂደትም ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ስለመሆኑ የገለፁት ምክትል አስተዳዳሪው በበጋ መስኖ ልማት በተከናወነው ስራ የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ዘጋቢ: ሪባቶ ቡሴር – ከሆሳዕና ጣቢያችን