በዘንድሮው ዓመት ከ4 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን በዳውሮ ዞን የኢሠራ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ

በዘንድሮው ዓመት ከ4 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን በዳውሮ ዞን የኢሠራ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ

በወረዳው ወደ 12 ሺህ የሚጠጋ ሄክታር በቡና ማሳ መሸፈኑም ተጠቁሟል።

በወረዳው ያለው የአየር ሁኔታ ለቡና ምርት ምቹ በመሆኑ በሁሉም ቀበሌያት ቡና በስፋት ይመረታል ተብሏል።

በዚህም ከ11 ሺህ 8 መቶ 38 ሄክታር በላይ መሬት በቡና ምርት መሸፈኑን የወረዳው ግብርና አካባቢ ጥበቃና ሕብረት ስራ ልማት ጽ/ቤት ምክትል ሀላፊና የእርሻ ዘርፍ ሀላፊ አቶ በቀለ አስፋው ገልጸዋል።

በወረዳው የቡና ምርት መጠን ከፍ ለማድረግ በዘንድሮው አመት 4 ሚሊዮን 1 መቶ 20 ሺህ የቡና ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ስራው በትኩረት እየተሰራ እንዳለ ሀላፊው አስረድተዋል።

ይህንን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ በአርሶ አደሮች፣ በወጣቶች አደረጃጀት፣ በአባቶች አደረጃጀትና በኢንቬስተሮች አማካይነት ቡና በስፋት እየለማ እንደሚገኝ አቶ በቀለ አብራርተዋል።

ለዚህ ተግባር የሚሆን የቡና ችግኝ በዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮጀክት አማካይነት እና በተጨማሪ በአራት ቀበሌያት በሚገኙ ችግኝ ጣቢያዎችም የማፍላት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሚያዝያ እና በሰኔ ወር ለሚካሄደው የተከላ ስራ በአሁኑ ሰዓት የጉድጓድ ቁፋሮ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አቶ በቀለ አመላክተዋል።

አቶ ደጀኔ ደሬቻ የሀጋል 02 ቀበሌ በቡና ችግኝ ጣቢያ ባለሙያ ሲሆኑ ጣቢያው ከዚህ በፊት በርካታ የቡና ችግኞችን በማፍላት የአካባቢው አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረጉ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አሁን ደግሞ ለዘንድሮ ዓመት ተከላ የሚውል ከ100 ሺህ በላይ የቡና ችግኞችን በጣቢያው የማዘጋጀት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢሠራ ወረዳ ቡናን በማህበር ተደራጅተው ከሚያለሙት ማህበራት መካከል አንዱ የአቦ አባቶች ቡና አምራች ማህበር ነው።

የማህበሩ ሰቢሳቢ አቶ አስራት ጋሻው ማህበሩ በ20 ሄክታር መሬት ቡና እያለማ እንዳለ ተናግረው በዘንድሮ ዓመት ደግሞ ተጨማሪ በ8 ሄክታር መሬት የቡና ችግኝ ለመትከል ከወዲሁ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚህም የማህበሩ አባላት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን በመጥቀስ።

ዘጋቢ፡ አማኑኤል ተገኝ – ከዋካ ጣቢያችን